ፋታህና ሀማስ በ2018 መጨረሻ በፍልስጤም አጠቃላይ ምርጫ እንዲካሄድ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍልስጤም ተፋላሚ ኃይሎች ፋታህና ሀማስ በ2018 መጨረሻ አጠቃላይ ምርጫ እንዲካሄድ ተስማምተዋል።

ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በካይሮ ያደረጉትን ድርድር ሲያጠናቅቁ ባወጡት መግለጫ፥ ለፕሬዚዳንታዊ እና ህግ አውጪዎች ምርጫው የፍልስጤም ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚሽን ዝግጅቱን እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል።

ፋታህ እና ሀማስ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት (ፒ ኤል ኦ) ፍልስጤማውያንን የሚወክል ትክክለኛው ድርጅት ስለመሆኑ መስማማታቸውም ነው የተነገረው።

ሀማስ እና ፋታህ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር የአንድነት መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ስምምነቱ ሀማስ ትጥቅ ይፈታል ወይ የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎችን አለመመለሱ ነው የተነገረው።

 

 

 

ምንጭ፦አልጀዚራ