መገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ በምክንያት የሚያምን ህብረተሰብ የማነጽ ኃላፊነት አለባቸው- ዶክተር ነገሪ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) መገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሮች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማሰራጨት ምክንያታዊ ህብረተሰብ እንዲፈጠር መስራት ቀዳሚ ተልዕኳቸው መሆኑን የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ሀገር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን የጋራ ምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንዳሉት፥ መገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉትን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች በማጠናከር በኩል የማይተካ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛል።

የዘርፉ ዋነኛ ተልዕኮም በሚያደርሰው ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ምክንያታዊ ህብረተሰብ በመፍጠር ለሰላም፣ለፈጣን ልማትና ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ ህዝቡን ዋነኛ ተዋናይ ማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት በሀገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንና ገጽታዋም በፍጥነት እየተለወጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሃላፊ ሚኒስትሩ ሰላም ለሃገራችን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የኮሙዩኒኬሽንና መገናኛ ብዙሃን ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የመጡ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አመራሮች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።