ሳሳካዋ ግሎባል በአራት ክልሎች ከ17 ሺህ በላይ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 10 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳሳካዋ ግሎባል 2 ሺህ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች ከ17 ሺህ በላይ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገለጸ።

ድርጅቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች በ118 የገበሬ ማህበራት ባከናወንኩት የግብርና የሙከራ ፕሮጀክት ነው አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረኩት ብሏል።

በዛሬው እለትም ከሻሸመኔ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በልዩ ፍጋፍ ተጠቃሚ የሆኑ የስጋ ደዌ ተጠቂ የግብርና ባለሙያዎችን ክንውን ጎብኝቷል።

የድርጅቱ የገበሬዎች አቅም ግንባታ አስተባባሪ አቶ አዚዝ ሽኩር፥ ድርጅቱ በሻሸመኔ እና አላማጣ በሚገኙ ሁለት የስጋ ደዌ ተጠቂ አርሶና አርብቶ አደር ማህበራት ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ድጋፉ በዋናነት ንብ ማነብ፣ የእርሻ ስራ፣ ከብት ማድለብና ንግድ ላይ ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአመራር፣ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግም ከ200 በላይ ለሆኑ የስጋ ደዌ ተጠቂ አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የሙከራ ፕሮጀክቱ በቀጣዩ ወር የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ ፕሮጀክቱን ለማራዘም ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሳሳካዋ ግሎባል በጃፓናዊው ዮኢሺ ሳሳካዋ የተመሰረተ ምግባረ ሰናይ ተቋም ነው።

 

በሃይለሚካኤል አበበ