ኢትዮጵያ መሰረታዊ አገልግሎትን በፍትሃዊነት በማድረሱ አፈፃፀሟ እየተሻሻለ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመሰረታዊ አገልግሎት በፍትሃዊነት እና በጥራት ተደራሽ የማድረጉ ስራ አፈፃፀም የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አለም አቀፍ ተቋማት አስታወቁ።

አራተኛ ዙር የደረሰው የመሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽነት መርሃ ግብር በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የውሃ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ መንገድ እና ግብርና ልማት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ የሚያደረግ ነው።

በየዙሩ ለአራት ዓመታት ለሚቆየው መርሀ ግብር ተፈፃሚነት የኢትዮጵያ መንግስት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ፥ ለፕሮጀክቶቹ ውጤታማነት የአለም ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ እና የብሪታንያ አለም አቀፍ ልማት ዲፓርትመንት በአጋርነት ድጋፍ ያደርጋሉ።

ድርጅቶቹ እና ተቋማቱ የልማት ፕሮግራሞቹን ለመደገፍ በየዓመቱ ከ500 እስከ 600 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የፋይናስ አቅርቦት እገዛ ያደረጋሉ።

እነዚህ ድርጅቶችና ተቋማት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባላቸው ስምምነት የፕሮጀክቱን አፈፃፀም በየስድስት ወሩ እየገመገሙ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ ይለቃሉ።

በዚህም የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ዛሬ ከባለድረሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ግምገማ ለልማት ፕሮግራሞች የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለሚፈለገው ዓላማ መዋላቸው የተገመገመበት ነው።

በግምገማው መሰረት የፕሮግራሙ አፈፃፀም በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉትን የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ በቀጣዮቹ አምስት አመታት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

በጤና፣ ትምህርት፣ ውሃ፣ መንገድ እና ግብርና ባለፉት ስድስት ወራት ለማከናወን የታቀዱ ተግባራት በስኬት ተጠናቀዋል ያሉት አቶ አድማሱ፥ በተለይም የወረዳዎችን አቅም የማጎልበቱ ስራ ውጤታማ ነበር ብለዋል።

በግምገማ መደረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ሀላፊ ተወካይ ጂኔቭራ ለቲቪያ፥ የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም በትምህርት እና ጤና ዘርፎች ጠንካራ የመረጃ ስርዓት በመዘርጋት ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

በትምህርት እና በጤናው ዘርፍ በፌዴራል፣ በክልሎች እና ወረዳዎች ደረጃ የመረጃ አያያዝ ስርዓቱ ምን እንደሚመስል ባለፈው ወር የመስክ ምልከታ መደረጉንም ነው ያነሱት።

በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ መላኩ ክፍሌም፥ በግምገማው በአምስቱ ዘርፎች እንዲከናወኑ ለጋሽ ድርጀቶች እና መንግስት የደረሱባቸው ስምምነቶች ተፈፃሚነት በጥልቀት ይታያል።

ጀነራል ኦዲተር መስሪያ ቤት፣ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ እና ሌሎች ተቋማት የእቅዶችን አፈጻፀም በገለልተኝነት አጣርተው ማረጋገጫ እንደሚሰጡም አቶ መላኩ ተናግሯል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጥናትና ፕላን ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ ጥጋቡ፥ በጤናው ዘርፍ የ20 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ለዜጎች ሁሉን አቀፍና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት አየተሰራ ነው ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ የልማት እቅድ ለሽፋን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፥ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ጤና ጣቢያዎች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።
ከተደራሽነት ቀጥሎ ጥራቱን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።

ዜጎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የጤና አግልግሎቶችን እንዲያገኙ እየተሰራ ቢሆንም በቂ አይደለም ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፥ ለአብነትም የቤተሰብ ምጣኔ እና የወሊድ አገልግሎት በነፃ ቢቀርቡም በሀብት የተሻሉት ናቸው ተጠቃሚ የሚሆኑት ብለዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የእቅድ ዝግጅት እና ሀብት ማፈላለግ ዳይሬክተሩ አቶ ኤሊያስ ግርማ፥ ሚኒስቴሩ በፕሮግራሙ የመረጃ ስርዓቱን ለማዘመን ለትምህርት ቤቶች ኮምፒውተሮች እና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲቀርብ እያገዘ ሲሆን፥ ይህም ትምህርት ቤቶች በስኩል ግራንት በቀጥታ ገንዘቡን ማግኘታቸው የፋይናንስ አቅማቸውን እያሳደገ ነው ብለዋል።

አቶ ኤሊያስ ባቀረቡት ሪፖርት በ2009 ዓመተ ምህረት 5ኛ ክፍልን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች ሀገራዊ አማካይ 85 ነጥብ 19 በመቶ መድረሱን ጠቁሞው፥ 8ኛ ክፍልን የሚያጠናቅቁት ደግሞ 54 ነጥብ 14 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበም ፕሮግራሙ ግልፀኝነትን እና ተጠያቂነትን ያሰፈነ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በፋሲካው ታደሰ