በደብረ ብርሃን ተደጋጋሚ ወንጀል ነዋሪውን ስጋት ውስጥ ጥሏል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደብረ ብርሃን ከተማ እየተስተዋለ ባለው የፀጥታ ችግር ዙሪያ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች እንድተናገሩት፥ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ተደጋጋሚ ወንጀሎች መበራከታቸው ለነዋሪው ስጋት ሆኗል ብለዋል።

በምሽት እንደልብ መንቀሳቀስ አልተቻለም የሚሉት ነዋሪዎቹ፥ የፖሊስ የላላ የክትትል ስርዓት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ከህብረተሰቡ ጋርም አለመቀናጀታቸውን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈፀመ ያለው የግድያ ወንጀል እያደገች ለመጣችው ደብረ ብርሃን ከተማ ፈተና መሆኑን አንስተዋል።

ነዋሪዎቹ በተለይ የቤት አከራዮች የሚያከራዩትን ነዋሪ እየለዩ አለመሆኑ ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም፥ ጉዳዩ ለፀጥታ አካላት ብቻ የሚተው እንዳልሆነ ነው የገለፁት።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በደብረ ብርሃን ከተማ የግድያ ወንጀል መበራከቱን ገልፀው፥ የተፈጠረው ሰሞነኛ ችግርም ከህብረተሰቡ የሚያልፍ ባለመሆኑ ተነጋግረን እንፈታዋለን ብለዋል።

በተለይም ችግሩን ለመፍታት የፀጥታ ሃይሉን ቁጥር በመጨመር እናጠናክራለን ነው ያሉት።

ከሚፈፀሙ ወንጀሎች ጀርባ የከተማዋን ሰላም የማይፈልጉ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ ገዱ፥ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ የምርመራ ስራ በፖሊስ እንደሚሰራ አንስተዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከመብራት መጥፋት ጋር በተያያዘ የተነሳው ችግር አመራሩ ምላሽ ባለመስጠቱ ቢሆንም፥ ንብረት መውደም አልነበረበትም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

በወረዳው የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ላይ የደረሰው ቃጠሎም ህዝቡን የማይወክል መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይቱ ላይ በርካታ የልማት ጥያቄዎች ለርዕሰ መስተዳድሩ የተነሱ ሲሆን፥ ቀዳሚው ጉዳይ ሰላም በመሆኑ ሰላምን እየጠበቅን የተነሱ ችግሮችን ሳይውል ሳያድር እንፈታለን ብለዋል።

 

 

 

 

በአላዩ ገረመው