አሜሪካ የአውሮፓ ህብረት በኢራን ላይ የሚጥላቸው ማአቀቦችን በደስታ እንደምትቀበል ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ኢራን በባለስቲክ ሚሳይል መርሃ ግብሯ ዙርያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ግጭቶች ውስጥ ካላት ሚና ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ህብረት የሚጣልባት አዳዲስ ማእቀቦችን እንደምትደግፍ አስታወቀች።

ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የከፋ ጠንካራ አቋም በኢራን ላይ ያላቸው ዶናልድ ትራምፕ፥ ቴሂራን እያከናወነች ላለችው የሚሳኤል መርሃ ግብር እና በየመን እና በሶሪያ ግጭቶች ውስጥ ላላት ሚና እንድትቀጣ ይፈልጋሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ትራምፕ በአውሮፓያኑ 2015 ኢራን የኑክሌር መርሃ ግብሯን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከምእራባውያኑ ጋር የገባቸውን ስምምነት ለማፅደቅ ፈቃደኛ አይደሉም።

የአሜሪካ ኮንግረስ የተገባውን የኑክሌር ስምምነት መሰረት በማድረግ ከኢራን ላይ የተነሱ የኢኮኖሚ ማእቀቦች በድጋሚ እንዲጣሉ ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።

የኑክሌር ስምምንቱ እንዲደረስ በብርቱ የሰራው የአውሮፓ ህብረት ስምምነቱ በህይወት እንዲቆይ ፍላጎት ያለው ሲሆን፥ የኢራን የሚሳኤል መርሃ ግብር እና በቀጠናው ግጭት ውስጥ ያላት ሚና ተለይቶ እንዲታይ ይፈልጋል።

በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት አድርገው የነበሩት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የቴሂራን የሚሳኤል መርሃ ግብር እንዳሳሰባቸው በመግለፅ አዲስ ማእቀብ ሊኖር እንደሚችል አስታውቀዋል።

የዋሽንግተን አስተዳደር የአውሮፓ ህብረት አዳዲስ ማዕቀቦችን በኢራን ላይ ቢጥል ደስተኛ እንደሚሆን በመግለፅ መጣሉ ገንቢ መሆኑን ነው ያስታወቀው።