ጠ/ሚ ኃይለማርያም ከኳታሩ ኤሚር ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ከትላንት ጀምሮ ኳታር ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ውሏቸው ከኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ኢትዮጵያ ለምታደርገው የልማት እንቅስቃሴ ኳታር ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል።

የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ በበኩላቸው፥ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል፡፡

ኳታር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ በመሆኑ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ዕድሎችን መጠቀም ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

ኤሚሩ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ለምታደርገው አስተዋፅኦ ኳታር ታላቅ አክብሮት እንዳላት ገልፀው፥ “ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋራችን ናት” ነው ያሉት፡፡

Hailemariam_Quatar.jpg

ኢትዮጵያ ለምትከተለው በመርህ ላይ የተመሰረተው ፓሊሲዋ ሀገራቸው ከበሬታ ያላት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በኢንቨስትመንት እና በተለያዩ መስኮች ለመተባበር ስምምነት ተፈራርመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የኳታርን ፋውንዴሽንንም ጎብኝተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኳታር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ነገ የመስክ ጉብኝት በማድረግ የሚጠናቀቅ መሆኑን፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም መግለፃቸው ይታወሳል።