በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ የተሽከርካሪ አደጋ የ21 ሰዎች ህይወት አጠፋ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ፥ ትናንት በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ የ21 ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

አደጋው የደረሰው የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3- 01758 ትግ የሆነው መለስተኛ አውቶቡስ የመጫን አቅሙ 21 ሆኖ ሳለ፥ 13 ሰዎችን በትርፍ ጭኖ በመጓዝ ላይ እንዳለ ነው፡፡

ተሸከርካሪው ወደ ሳዕሲዕ ፃዕዳ እምባ ወረዳ ለቀብር የሚሄዱ ሰዎችን አድርሶ ሲመለስ አፅቢ ወንበርታ ወረዳ ልዩ ቦታ አፅገበት የተባለው ስፍራ ሲደርስ በመገልበጡ አደጋው ሊደረስ ችሏል፡፡

የአፅቢ ወንበርታ ወረዳ ትራፊክ ፖሊስ አስተባባሪ ኢንስፔክተር ገብረመድህን ንርአ፥ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለለፁት በአደጋው ሾፌሩን ጨምሮ የ21 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ አልፏል።

እንዲሁም አምስት ሰዎች ከባድ፣ አንድ ሰው ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ መቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል እና ውቕሮ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

አንድ ህፃን እና ሌሎቹ ቀሪ ሰዎች የአካል ጉዳት ሳይደርስባቸው መትረፋቸውን ኢንስፔክተሩ ጠቅሰው፥ የሟቾቹን አስክሬን ቤተሰቦቻቸው እንዲረከቡ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡