ጠ/ሚ ኃይለማርያም በኳታር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኳታር ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ከትላንት ጀምሮ ኳታር ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ የስራ ጉብኝታቸው ኢትዮጵያውያኑን አነጋግረዋል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ኢትዮጵያውያኑ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነው፥ ይኸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስትም ለኮሚኒቲው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ለነበረው ግጭት ሰላም ማስፈን እንደተቻለ እና የበለጠ ለማረጋጋት መንግስት ከህዝቡ ጎን ሆኖ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ እድገት በአማካይ 10 ነጥብ 9 በመቶ ማደጉንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በበኩላቸው መንግስት በሳዑዲ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ላደረገው ጥረት አመስግነዋል።

የኮሚኒቲ ትምህርት ቤት በኳታር ለመክፈት እንዲቻል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያውያኑ አገሪቱ ውስጥ ያለውን እድገትም አድንቀዋል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ከዱሃ በስልክ ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ዛሬ እና ነገ በሚኖራቸው ቆይታ በንግድ እና ኢንቨስትመንት በተለይም የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ለኳታር ገበያ በሚቀርቡበት ሁኔታ ላይ ውይይት ይደረጋል።

በትላንቱ ውሎም ከኳታሩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙርያ ውይይት መደረጉን ቃል አቀባዩ አስታውሰዋል።

የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ መዋለ ንዋያቸወን እያፈሰሱ ነው፤ ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች አኳያ በቀጣይም ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ይታመናል።

በዚህም ዛሬ ለኳታር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙርያ ለአምሰት ሰዓታት ያህል ማብራሪያ እና ገለፃ ይደረግላቸዋል ሲሉ ቃል አቀባይ መለስ ገልፀዋል።

በዚህ ጉብኝት ውስጥ ኢትዮጵያ እና ኳታር በቀጣናው ስለሚኖራቸው የጋራ ትብብር ላይም ሁለቱ መሪዎች ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የኳታር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ነገ የመስክ ጉብኝት በማድረግ የሚጠናቀቅ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

 

 

በስላባት ማናየ