ብአዴን ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ጥቆማ የተደረገባቸውን አመራሮች ተጠያቂ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ጥቆማ የተደረገባቸውን 857 መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በማጣራት ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን እንዳሉት፥ ብአዴን በተለይ ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ ከባድ ጥርጣሬ አሳድሮ ስለነበር ችግሩን ለማጣራት ሰፊ ሥራ ሰርቷል።

አመራሩን ፊት ለፊት ከመገምገምና ከማስተካከል በተጨማሪም የእውነት አፈላላጊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በልዩ ሁኔታ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ግብረ ኃይሉ የደረሱትን 857 ጥቆማዎችን የማጣራት ሥራ መሰራቱንም አቶ አለምነው ጠቁመዋል።

በዚህም ግብረሃይሉ ከደረሱት 857 ጥቆማዎች ውስጥ 117 የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት መሬት ያለአግባብ በመውሰድ፣ ከግብር ስወራና በዝምድና ከመቅጠር ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ መግባታቸው ተረጋግጧልም ነው ያሉት።

ጥቆማ ከተደረገባቸው 740 መካከለኛ አመራሮችም 355ቱ መሬትን ደራርበው በመውሰድና በመሰል ችግሮች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በሙስና ችግር ውስጥ የተገኙትን ከኃላፊነት ቦታቸው የማንሳትና ዝቅ ብለው እንዲመደቡ እንዲሁም በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ እየተደረገ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።