በመላ ሃገሪቱ 10 የፊዚዮ ቴራፒ የህክምና ማዕከላት እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን ቁጥራቸው124 የሚሆኑ የመንግስት የህክምና መስጫ ሆስፒታሎች ቢገኙም ፥በአጠቃላይ የፊዚዮ ቴራፒ አገልግሎት የሚሰጡ ሙያተኞች ግን 500 ብቻ ናቸው።

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ እንኳን በአሁኑ ጊዜ 320 የሚሆኑ ታካሚዎች በ10 ፊዚዮ ቴራፒስት ባለሙያዎች ሲታከሙ፤ ቁጥራቸው 50 የሚሆኑ የፊዚዮ ቴራፒ ታከሚዎች ደግሞ በየቀኑ የህክምና ተቋሙን ይረግጣሉ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቅርቡ ያጠናው ጥናት ለእጥረቱ  ዋነኛ ምክንያት ሙያተኞች በሚፈለገው ደረጃ አለመሰልጠናቸውና የህክምና ቁሳቁሶችም ቢሆኑ በሚፈለገው መጠን አለመሟላታቸው እንደሆነ  ይገልፃል።

የፊዚዮ ቴራፒ ህክምናቸውን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፣ በዘውዲቱና በተለያዩ ሆስፒታሎች እየተከታተሉ የሚገኙ ታካሚዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በተቋማቱ በቂ የሚባል የህክምና ባለሙያዎችና ቁሳቁሶች ሊሟሉ ባለመቻላቸው በቂ ህክምና እያገኙ አለመሆኑን ይናገራሉ።

ችግሩ ከዚህም በላይ ነው የሚሉት ታካሚዎች ፥ የሙያተኞችን ጥምርታ ከተካሚው አንጻር ሲታይ እጅግ አናሳ በመሆኑ  ህመማችን እየተባባሰብን መጥቷል ነው የሚሉት።

ችግሩ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታካሚዎች ዘንድም ጎልቶ መታየቱን የሚናገሩት ደግሞ በሆስፒታሉ የፊዚዮ ቴራፒ ህክምና ክፍል ሃላፊ  ዶክተር ካቪታ ቲሩቡቫን ናቸው።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና መድህን ህክምና አገልግሎትና ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጼጥሮስ ኪዳኔ በበኩላቸው ፥ ችግሩን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሃገር አቀፍ ደረጃ መፍታት የሚያስችል ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የፊዚዮ ቴራፒ መስጫ ማዕከላት መገንባታቸውንና በቁሳቁስ ደረጃም ቢሆን  የሚታዮ ክፍተቶችን መሙላይት የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በሙያተኖች ደረጃ የሚስተዋለውን እጥረት  ለመቅረፍም ራሱን የቻለ የትምህርት ክፍል እንዲቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያወሱት።

በዘርፉ የሚታየውን ስር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ በየተቋማቱ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል ከቻሉ ፥ የህክምና እጥረቱንም ይሁን በባለሙያዎች ዘንድ የሚታየው ክፍተት በቅርብ ጊዚያቶች ይቀረፋል እንደ ሃላፊዎች ገለፃ።
 

በሰለሞን ሃይለኢየሱስ