በአዳማ ከተማ የክፍለ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዳማ ከተማ የክፍለ ከተማ አስተዳደር አሰራር ተግባራዊ ሆነ።

በ18 የቀበሌ አስተዳደሮች ተዋቅራ የነበረችው የአዳማ ከተማ አሁን በ6 ክፍለ ከተሞች ተዋቅራ ወደ ስራ ገብታለች፡፡

ስድስቱም ክፍለ ከተሞች የአካባቢው ማህበረሰብ ይጠቀምበት ከነበረው ስያሜ መጠሪያቸውን አግኝተዋል ነው የተባለው።

የከተማው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚኤሳ ኤሌማ እንደገለፁት፥ አዳማ የንግድ፣ የኮንፈረንስና የቱሪዝም ማዕከል መሆኗ ብሎም የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች በከተማዋ ላይ መታየታቸው በክፍለ ከተማ አስተዳደር እንድትዋቀር ምክንያት ሆኗል፡፡

ለማህበራዊ እንቅስቃሴ ቁልፍ የሆኑ ዘጠኝ ሴክተሮችም ወደ ስድስቱ ክፍለ ከተሞች እንዲወርዱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

18 የቀበሌ አስተዳደርን በአንድ ከንቲባ መምራት አስቸጋሪ ነው ያሉት ሃላፊው፥ አሁን ላይ 6 የስራ አስፈፃሚዎች በክፍለ ከተማ መመደባቸው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ዘገባውን የአሰላ ፋና ኤፍ ኤም ባልደረባችን ኤርሚያስ ቦጋለ አድርሶናል።