በ400 የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ181 ሚሊየን ዶላር መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገር አቀፍ ደረጃ በ400 የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ181 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።

ገንዘቡ የአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) የእናቶችና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ ለሚያከናውናቸው አራት መርሃ ግብሮች ትግበራ የሚውል ነው ተብሏል።

ለመርሃ ግብሮቹ ትግበራ የኮሪያ አለም አቀፍ የትብብር ድርጅት (ኮይካ) ድጋፍ ያደርጋል።

መርሃ ግብሮቹ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና ክብካቤ፣ የአዳጊ ክልሎች የጤና ስርዓት፣ ለንፅህና ትኩረት ለሚሰጠው የዋሽ ፕሮግራም እንዲሁም የክትትልና ግምገማ ተሞክሮና ስርፀት ስራዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በዩ ኤስ ኤይድ ይፋ የተደረገው መርሃ ግብር በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች፥ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት እንዲሁም የህፃናት ጤና አገልግሎትን ለማዳረስ እንደሚውል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ተናግረዋል።

181 ሚሊየን ዶላሩ ከያዝነው የአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በቀጣዮቹ አምስት አመታት እንደሚለቀቅም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

 


በኤርሚያስ ፍቅሬ