በግብፅ ሲናይ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት የ6 ወታደሮች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታጣቂዎች በግብፅ ሲናይ በረሃ የፍተሻ ጣቢያ አቅራቢያ በድንገት በከፈቱት ተኩስ የስድስት ወታደሮች ህይወት ማለፉን የግብፅ ጦር አስታወቀ።

በግብፅ እስላማዊው መሪ መሀሙድ ሙርሲ ከስልጣን ከወረዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2013 ወዲህ በፀጥታ ሀይሎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃት እየተበራከቱ መጥተዋል።

የግብፅ ጦር ባወጣው መግለጫ፥ የጦር መሳሪያ የታጠቁ አሸባሪዎች በአሪሽ ከተማ የሚገኝ የፍተሻ ጣቢያ ላይ የእጅ ቦምብ እና የጦር መሳሪያ በመጠቀም ነው ጥቃቱን ያደረሱት ብሏል።

በጥቃቱም የስድስት ወታደሮች ህይወት ሲያልፍ አራት ወታደሮች ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱም በመግለጫው ላይ ተብራርቷል።

በአሁኑ ጊዜም የግብፅ የፀጥታ አካላት ጥቃት ፈጻሚዎቹን በማፈላለግ ላይ መሆናቸውም ተነግሯል።

ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ለ30 ደቂቃ ያክል በነረው የተኩስ ልወውጥ ሁለቱ የአሸባሪው ቡድን አባላት መገደላቸውንም የግብፅ ጦር አስታውቋል።

ግብፅ በአሁኑ ጊዜ በሲናይ በረሃ ውስጥ ከአሸባሪው አይ ኤስ ጋር ግንኙነት ካላቸው አሸባሪዎች ጋር ውጊያ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ምንጭ፦ www.reuters.com