ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ ትብብር ሊቀመንበር ሆነች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ለቀጣይ አንድ ዓመት የዓባይ ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍን በሊቀመንበርነት እንድትመራ ተመረጠች።

በኡጋንዳ ኢንቴቤ በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ኢትዮጵያ የሊቀመንበርነቱን ቦታ ከኡጋንዳ የተረከበች ሲሆን፥ ለአንድ ዓመት ያህል የትብብሩን የሚኒስትሮች ምክር ቤትና የናይል የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴን ትመራለች።

በስብሰባው ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ የቡሩንዲ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ታንዛኒያ የውሃ ሚንስትሮች፣ ባለሥልጣናት እንዲሁም ተወካዮች ተገኝተዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን  ወክለው ሚንስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ገርባ ለአንድ ዓመት የሚቆየውን የሊቀመንበርነት ሥልጣን ከኡጋንዳ አቻቸው ሳም ቻፕቶሪስ ተረክበዋል።

የትብብሩ ከፍተኛው የሥልጣን ባለቤት የሆነው የሚንስትሮች ምክር ቤት የናይል ተፋሰስን ፖለቲካዊና ልማታዊ ጉዳዮች በበላይነት ይመራል።

የናይል የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ ለአንድ ቀን ባካሄደው ስብሰባም ግብፅ በማዕቀፉ ያላትን ተሳትፎ በሚመለከት ፍሬያማ ውይይት መደረጉ ተገልጿል።

የሚንስትሮች ምክር ቤት የትብብሩ የ10 ዓመት ስትራቴጂ ማፅደቁም ተገልጿል።

የኃይል ልማትና የኃይል ንግድን ማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንዲሁም በተፋሰሱ አካባቢ ያለውን የአካባቢ ጥበቃ ሥርዓት መጠበቅና መንከባከብ ደግሞ የስትራቴጂው ቀዳሚ አጀንዳዎች ናቸው።

አባል አገራቱ በየዓመቱ እየተፈራረቁ በሚመሩት የአባይ ትብብር ማእቀፍ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ የሊቀመንበርነትን የምትቀበል ሀገር ከአንድ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ በሚካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ይታወቃል።

ምንጭ፦ ኢዜአ