የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቃዋሚዎች ጋር በጁባ እየመከሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቃዋሚዎች ጋር በጁባ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ የሱዳን፣ የኬንያ፣ የዮጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የጅቡቲና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች ተገኝተዋል።

የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ በደቡብ ሱዳን ያለው አለመረጋጋት በዘላቂነት እስኪፈታ ኢጋድ ጥረቱን ይቀጥላል ብለዋል።

የተለያዩ ወገኖች የተሳተፉበት በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ እየተካሄደ ያለው ስብሰባ ስኬታማ መሆኑንም ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል።

በጁባ፣ ካርቱም፣ አዲስ አበባ፣ እና በፕሪቶሪያ በተደረጉት ውይይቶች የአገሪቱ የቀድሞ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሪክ ማቻርን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች የሰላም ሂደቱ እንዲፋጠን ፍላጎታቸው መሆኑን ለማወቅ መቻሉን አስረድተዋል።

ዶክተር ወርቅነህ፥ የኢጋድ አባል አገራት የአዲስ አበባው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ድጋፍ ቢያደርግም ዋነኛ ፈጻሚዎቹ ግን የደቡብ ሱዳን ህዝብና መንግስትና ናቸው ብለዋል።

በዛሬው ስብሰባ የደቡብ ሱዳን መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ፍላጎት እንዳለው ማረጋገጡን ዶክተር ወርቅነህ ገልፀዋል።

ስብሰባው ዶክተር ወርቅነህ በሊቀ መንበርነት ሲመሩት የደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርቲን ላምሮ በምክትል ሊቀመንበርነት ይመሩታል።

የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቀደሞ ሲልም ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሄድ ከቀድሞ የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሬክ ማቻር ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡

ለደቡብ ሱዳን መረጋጋት የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ አገሪቱ ሰላማዊ እንድትሆን ኢጋድ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።