በካሊፎርኒያው የሰደድ እሳት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርኒያ ግዛት የተነሳው ሰደድ እሳት ህይወታቸውን የቀጠፈባቸው ሰዎች ቁጥር 31 ደርሷል።

በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች የገቡበት አለመታወቁን የሚገልፁት የአከባቢው ባለስልጣናት፥ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ነው እየተናገሩ ያሉት።

ሰደድ እሳቱ እስካሁን 3 ሺህ 500 ቤቶችን ያወደመ ሲሆን፥ 25 ሺህ ሰዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።

ከአውሮፓውያኑ 1933 በኋላ ካሊፎርኒያን ያጋጠማት የከፋ ነው የተባለውን ይህን ሰደድ እሳት በቁጥጥር ስር ለማዋል 8 ሺህ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተሰማርትዋል።

በግዛቲቱ የሚገኙ ሰደድ እሳቱ የደረሰባቸው ከተሞች ተጨማሪ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ሰዎችን ከመኖሪያቸው አሽሽተዋል።

እሳቱን ያባባሰው ሀይለኛ ንፋስ ባለፉት ቀናት ጋብ ቢልም ዛሬ ጠንካራ ንፋስ ይኖራል የሚለው ትንበያ ስጋትን ፈጥሯል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ