በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አከባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ ተብለው ከሚጠሩ ህገወጥ ተግባራት ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ የክልሉ መንግስት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010( ኤፍ. ቢ. ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህብረተሰቡ በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ ተብለው ከሚጠሩት ህገወጥ ተግባራት ራሱን እንዲጠብቅ አሳሰበ።

ሰሞኑን በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች የወጣቶችን ስሜት ባላስፈላጊ መንገድ በመቀስቀስ የተካሄዱ ሰልፎች የክልሉን ህዝብ ፍላጎት ያላገናዘቡ እና የማይገልፁ መሆናቸውን የክልሉ መንግሥት ገልጿል ።

የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዬች ቢሮ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ የክልሉ መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይሁንና ሰሞኑን በቢሾፍቱ እና ቡራዩ ከተሞች በተከበሩ የኢሬቻ በዓላት ላይ አባ ገዳዎች ያስቀመጡትን የበዓሉን ስነስረዓት በመጣስ የሁከት መልዕክቶች ሲተላለፉ እንደነበር ጠቅሰዋል ።

ከሁከት ተግባራት በተጨማሪ ህገወጥ ሰንደቅ ዓላማዎችን ሲጠቀሙ እንደነበር አቶ አዲሱ ተናግረዋል።

ላለፉት ቀናት ደግሞ ህገወጦች የወጣቱን ስሜት በመቀስቀስ በሻሸመኔና በምዕራብ ሀረርጌ ቡኬ ወረዳ የሰዎች ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነዋል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ ራሱን ከእነዚህ ተግባራት በመጠበቅ እና በመከላከል ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ።

 

በድጋፌ ዳኛቸው