ትራምፕ ኦባማ ኬር የጤና መድህን ፖሊሲን ውድቅ የሚያደርገውን ውሳኔ አሳለፉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 2 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአስፈፃሚነት ስልጣናቸውን ተጠቅመው የኦባማ ኬር የጤና መድህን ፖሊሲን ከአገልግሎት የሚያስወጣውን መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ፈርመዋል።

አስተዳደራዊ ፊርማቸውን ያስቀመጡበት አዲሱ የአሜሪካን የጤና መድህን መመሪያ አነስተኛ ጥቅም የሚያስገኙ የነበሩ የጤና መድህን ሽያጭ ፖሊሲዎችን ውድቅ የሚያደርግ ነው።

ትራምፕ ውሳኔውን ያሳለፉት ሪፐብሊካን የሚበዙበት የአሜሪካ ኮንግረስ፥ ኦባማ ኬርን ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ አያሳልፍም የሚል ፍርሃት ስላለባቸው ነው ተብሏል።

ፕሬዚዳንቱ ሶስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አዲሱን የጤና መድህን መመሪያ ለማስፈፀም ዝቅተኛ ወጪን፣ አጠቃላይ የጤና መድህን አገልግሎትን፣ እንዲሁም የአጭር ጊዜ የህክምና ሽፋንን በአማራጭነት ያካተቱ ደንቦችን እንዲያዘጋጁ አዘዋል።

በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት የጤና መድህን አገልግሎት ለመስጠት የተሰማሩ ተቋማት ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች አገልግሎቱን በማንኛውም አማራጭ የሚያቀርቡበት አሰራር ተመቻችቷል።

ይህ የትራምፕ ውሳኔ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በጋራ በመሆን መድህን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

አሰሪ ተቋማትም ሰራተኞቻቸው በጋራ የጤና መድህን ሽፋን እንዲያገኙ የሚያደርጉበት ሁኔታ የተመቻቸ ሲሆን፥ ሰራተኞችም ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የመድህን አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ ነው የተመለከተው።

አዲሱ መመሪያ ለመድህን አገልግሎት አቅራቢዎች ውድድርን የሚጨምር ሲሆን ለሀገሪቱ ዜጎች አማራጭ የጤና መድህን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ተነግሯል።

ትራምፕ በመመሪያው መንግስት ለተጨማሪ ወጪ አይዳረግም ብለዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ መመሪያው ለጤና መድህን የሚወጣውን ወጭ ለመቀነስ ያለመ ቁልፍ ውሳኔ ብለውታል።

በኦማባ ኬር ፖሊሲ የአጭር ጊዜ የጤና መድህን በ3 ወር ብቻ የተገደበ ነበር፤ ትራምፕ ግን ይህ አገልግሎት ወደ አንድ ዓመት ከፍ እንዲል አቅደዋል።

የመድህን ወጪን ቢቀነስም ለህክምና የሚደረጉ ወጪዎችን ሊጨምር እንደሚችልም እየተተቸ ነው።

 

 

 

 

ምንጭ፦ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ እና ሩሲያ ቱዴይ