መዲናዋ በሆቴሎች ግንባታ የተሻለ እድገት ብታሳይም ከአገልግሎት አኳያ ጉድለት እንዳለባት ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) አዲስ አበባ በሆቴሎች ግንባታ የተሻለ እድገት እያሳየች ቢሆንም ከአገልግሎት አኳያ ግን አሁንም ጉድለቶች እንዳሉባት ተነግሯል።

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴሩ በመዲናዋ ከሚገኙ ሆቴሎች የተወሰኑት የሚሰጡት አገልግሎት ዝቅተኛ መሆኑን እና ከሚሰጡት አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁ እንዳሉ ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአዲስ አበባ በየወሩ አንድ ሆቴል ተመርቆ ወደ ስራ የሚገባ ሲሆን፥ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ስምንት ሆቴሎችም በመዲናዋ ይገኛሉ።

ይህ የሚያሳየው ደግሞ በአዲስ አበባ በሆቴል ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች መበራከታቸውን እና ከተማዋም ለዘርፉ የሰጠችው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑ ነው።

አዲስ አበባ የምታስተናግዳቸው ጉባኤዎች እና ስብስባዎች በየጊዜው ቁጥራቸው እየተበራከቱ መጥተዋል ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ ሆቴል ዘርፍ በርካታ ጥናቶችን ያደረጉት ዶክተር አያሌው ሲሳይ፥ የሆቴሉ ዘርፍ እያደገ ቢመጣም አሁንም ሊታለፍ የሚገባ የአገልግሎት ጥራት መሰናክል መኖሩን ገልፀዋል።

የባልህ እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ እና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ገዛኽኝ አባተ፥ በአዲስ አበባ በሚገኙ የተወሰኑ ሆቴሎች የሚስተዋል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት።

እርሳቸው ለዚህ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ምክንያቱ ደግሞ የሰው ሃይል አቀጣጠራቸው ጉዳይ ነው ይላሉ።

በሆቴል ዘርፉ ላይ የሚሰማሩ ጥበቃዎች፣ አስተናጋጅ እና ዋና ስራ አስኪያጆች የምዘና ብቃት ማለፍ ቢኖርባቸውም፥ የተወሰኑ የመዲናዋ ሆቴሎች ከዚህ በተቃርኖ እየተጓዙ መሆኑን ሚኒስቴሩ ባደረገው ፍተሻ አረጋግጧል።

በዚህም የተነሳ ሚኒስቴሩ የወጡ ህጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ በየጊዜው ፍተሻ እያደረገ ሲሆን፥ በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላትም ከትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ ገዛኸኝ።

እርሳቸው “በጋራ እየሰራን ነው” ካሏቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ የሆቴል ባለቤቶች ማህበር አንዱ ነው።

ማህበሩ በዘርፉ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ለሆቴል ባለሙያዎች በየጊዜው ስልጠና እየሰጠ መሆኑን የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ሉድ አብይ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ የሚስተዋለውን ብቃት ያለው የሆቴል ባለሙያ ለማፍራት የሆቴል ባለሙያ ማሰልጠኛ ለማቋቋም ከውሳኔ ላይ ተደርሶ በአሁኑ ወቅት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተነግሯል።

ዶክተር አያሌው፥ ኢትዮጵያ የሆቴል አገልግሎትን ለማሻሻል የምትጠቀምበት ደረጃ የመስጠት ሁኔታ ጥሩ ቢሆንም የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው እንቀስቃሴ ውስጥ ደረጃው ከተሰጠ በኋላ ዞር ብሎ መገምገም ወሳኝ ነው ይላሉ።

አቶ ገዛኸኝ በበኩላቸው ይህን ሃሳብ በመጋራት በተወሰኑ ሆቴሎች የአገልግሎት ጥራት መጓደል ብቻ ሳይሆን፥ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪም ይታያል ብለዋል።

ይህን አካሄድ ለመግታት ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁሟል።

 

 

በስላባት ማናዬ