በጎዳና ላይ የሚገኙ ሴቶች እና ህፃናትን ወደ መደበኛ ኑሮ ለመመለስ እየተሰራ ነው-የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በጎዳና ላይ የሚገኙ ሴቶች እና ህፃናትን በመለየት ወደ መደበኛ ኑሮ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ጎዳና በወጡ ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለልም ጎዳና ላይ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሴቶች እና ህፃናትን ለይቶ በማንሳት በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬከተይ አቶ አለማየሁ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እስካሁን በአዲስ አበባ ብቻ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች እና ህፃናት ተለይተው ስልጠና ወስደዋል።

እድሜያቸው፣ የመጡበት ክልል እና የመኖሪያ ቀያቸው እንዲሁም የቤተሰቦቻቸው የኑሮ ደረጃን በመለየት ስልጠናውን በሀዋሳ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብተው እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት።

ስልጠና ከወሰዱት ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑት ህፃናት ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥ የቤተሰቦቻቸው የኑሮ ደረጃን በማጥናት ከ300 በላይ የሚሆኑ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል።

ስልጠናው ቀጣይ ህይወታቸውን ሊመሩባቸው የሚችሉባቸውን ጥበቦች እና ስራን ለመፍጠር የሚያግዟቸው መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ትምህርት መማር ያለባቸው ወደ ትምህርት እንዲገቡ ስራ መስራት የሚችሉት ደግሞ ወደ ስራ የሚሰማሩበት ሁኔታም ተመቻችቷል ነው የተባለው።

ይህንን እቅድ ወደ ተግባር ለማስገባትም ሚኒስቴሩ ባለፈው ዓመት ከክልሎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ክልሎችም ወደ ተግባር የገቡ መሆናቸውን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱን ከተፈራረሙት ክልሎች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ክልል ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ፥ ከባለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ከ3 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑ ሴቶች እና ህፃናትን ለይቻለሁ ሲል ገልጿል።

ክልሉ ለስራውም ከ31 ሚሊየን ብር በላይ አዘጋጅቷል።

በአዲስ አበባ ከተለዩት 12 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች እና ህጻናት በተጨማሪ በአራት ዙር ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ህጻናት በከተማዋ ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በመለየት ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀላቸው ተነግሯል።

 

በዙፋን ካሳሁን