ግብፅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በድጋሚ ለተጨማሪ ሶስት ወራት አራዘመች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለሁለተኛ ጊዜ ለተጨማሪ ሶስት ወራት ማራዘሟን ይፋ አደረገች።

ሀገሪቱ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈፀሙ ሁለት የቦምብ ጥቃት በትንሹ፥ 45 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣቷ ይታወቃል።

አዋጁ በሃምሌ ወር ለተጨማሪ ሶስት ወራት ተራዝሞ ነበር።

በፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ ኤል ሲሲ ውሳኔ ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፥ በመንግስት ይፋዊ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል።

ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የተራዘመው አዋጁ በሰባት ቀናት ውስጥ ለሀገሪቱ ፓርላማ ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።

በግብፅ ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ በኮፕትክ ክርስቲያኖች ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች ከ100 የማያንሱ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፥ በርካቶችም ተጎድተዋል።

 

 


ምንጭ፦ሬውተርስ እና ፎክስ ኒውስ