አሜሪካ ከዩኔስኮ አባልነት ወጣች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና  የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ አባልነት ራሷን እንደምታስወጣ አስታወቀች።

ዋሽንግተን ለዚህ ውሳኔዋ ምክንያት ያደረገችው “ድርጅቱ ፀረ እስራኤል የሆነ የአድሎ ድርጊት የሚፈፅም ነው” የሚል ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የድርጅቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው ፓሪስ ታዛቢ ብቻ እንደሚኖራት ነው ያስታወቀው።

በአውሮፓውያኑ 2011 ላይ ዩኔስኮ የፍልስጤም አስተዳደርን በአባልነት መቀበሉ ዩናይትድ ስቴትስን አስቆጥቶ ነበር።

በዚያው ዓመት ዋሽንግተን ለድርጅቱ የምታቀርበውን ፋይናንስ ያቋረጠች ቢሆንም፥ በይፋ ግን ከድርጅቱ አልወጣችም ነበር።

አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ድርጅቶች የፍልስጤም አስተዳደርን እንደ ሀገር ተመልክተው ምንም ዓይነት ድርጊት እንዳይፈፅሙ ትፈልጋለች።

አገሪቱ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች በፍልስጤም እና እስራኤል መካከል የሚደረጉ የሰላም ድርድር ውጤትን መጠበቅ አለባቸው ባይ ናት።

ዩኔስኮ በዓለም ዙሪያ ቅርሶች ተጠብቀው ዘመን እንዲሻገሩ የሚሰራ የተመድ አካል ሲሆን፥ በማደግ ላይ ባሉ አገራትም ትምህርት እንዲስፋፋ ድጋፍ ያደርጋል።

 

ምንጭ፦ አልጀዚራ እና ቢቢሲ