በምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ዛሬ ጧት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ 60 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ፥ በተቃራኒ አቅጣጫ ከሚመጣ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ነው አደጋው የደረሰው።

የደቡብ አቸፈር ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ዳኝነት ፈንቴ እንደገለጹት፥ የትራፊክ አደጋው የደረሰው በዱር ቤቴ ከተማ ማርያም ቤተክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡
በዚህም በአነስተኛ የህዝብ ማመላለሻው ከነበሩት 10 ሰዎች መካከል አሽከርካሪውንና ረዳቱን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች እና ከአውቶብሱ ደግሞ የአሽከርካሪው ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡
ከአነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪው አንድ ህጻን ልጅና ከአውቶብሱ ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው፥ በዱር ቤቴና በፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስቲታሎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ኢንስፔክተሩ ገልፀዋል።
በአደጋዉ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች አስክሬንም ቤተሰቦቻቸው እንዲረከቡ እየተደረገ ሲሆን የአደጋው መንስኤም እየተጣራ ነው፡፡
ምንጭ፦ኢዜአ