የቅጥር፣ የመብትና የወሊድ እረፍትን ጨምሮ ዝርዝር ጉዳዮችን በመያዝ የተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ማሻሻያ የተደረገበት የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ዝርዝር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ረቂቅ አዋጁ ነባሩን የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99ን ለመተካት የተዘጋጀ ነው።

ነባሩን አዋጅ ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ፣ ብቃት እና ስነምግባር የተላበሰ የፐብሊክ ሰርቪስ እንዲፈጠር ለማስቻል የሚለው ይገኝበታል።

ከዚህ ውጭ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚካሄደው ምልመላ እና የመረጣ ስርዓት በመሰረታዊነት በመለወጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሙያ እና የስራ ብቃት ማረጋገጫ አሰራር ለመዘርጋት የአዋጁ መሻሻል ማስፈለጉን በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

እንዲሁም በነባሩ አዋጅ የታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እና በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት እና የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ ነው ተብሏል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የመንግስት መስሪያ ቤት አደረጃጀትን፣ የስራ ምዘና፣ የደመወዝ ስኬል እና አበል፣ የስራ አካባቢ ደህንነት እና ጤንነት፣ መብት እና ግዴታዎች፣ የዲሲፕሊን እርምጃዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ተካተዋል።

በረቂቅ አዋጁ ተሻሽለው የቀረቡ እና አዲስ የተካተቱ ድንጋጌዎች ያሉ ሲሆን፥ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ወደ ፐብሊክ ሰርቪስ የሚገባበት አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ስርዓትን መዘርጋት እንደሚገባ በማሻሻያው ቀርቧል።

የጊዜያዊ ሰራተኛ ቅጥርን በተመለከተ በነባሩ ህግ የጊዜያዊ ሰራተኞች መብት እና ግዴታን በመመሪያ መወሰኑ በአፈፃፀሙ ላይ ክፍተት ሲፈጥር የነበረ በመሆኑ በሰራተኞች መብት አጠባበቅ ላይ ከፍተኛ ችግር ሲፈጥር መቆየቱ ተነስቷል።

በዚህም መሰረት በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ መሰረታዊ መብቶች እና ግዴታዎች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው በሚወጡ በአዋጅ ወይም በደንብ መመላከት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

ልዩ ሙያ እና እውቀት ያላቸውን ሰራተኞች የመንግስት መስሪያ ቤቶች በጋራ ቀጥረው በጋራ መጠቀም እንዲችሉ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት አስፍላጊ መሆኑም በድንጋጌው ተካቷል።

ምን ማሻሻያዎች ተደረጉ?

ይህም ተግባራዊ የሚሆነው የሰራተኛው ልዩ እውቀት እና ሙያዊ አቅም መስሪያ ቤቱ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ እንደሆነ እና የቅጥሩ ሁኔታ፣ የሚቆይበት ጊዜ፣ ደመወዝ አከፋፈል እና ሌሎች ሁኔታዎች ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ እንድሚወሰን በረቂቁ ላይ ተጠቅሷል።

ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በክፍት የስራ መደብ ላይ የደረጃ እድገት ሊሰጠው የሚችለው ከሌሎች መስፈርቶች በተጨማሪ ለስራ መደቡ ያለውን የብቃት ማረጋገጫ የማቅረብ ግዴታውን ሲፈፅም ይሆናል።

በነባሩ አሰራር ከአንድ ዓመት በላይ ለትምህርት ወይም ስልጠና የሄደን የመንግስት ሰራተኛ ለመተካት በተጠባባቂነት የሚመደቡ ግለሰቦች ለረዥም ጊዜ በስራ መደቡ ላይ ያለውድድር እንዲመደቡ መደረጉ ቅሬታ ሲያስከትል ቆይቷል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅም ማሻሻያ በማድረግ ምድባው ከገንዘብ እና ከጥቅማጥቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ በውሳኔ ብቻ ምድባውን ማካሄዱ ፍትሃዊ ባለመሆኑ በውድድር መፈፀም እንዳለበት ነው የተደነገገው።

አንድ የመንግስት ሰራተኛ ወደ ሌላ የመንግስት መስሪያ ቤት በሚዘዋወርበት ጊዜ እንድ አዲስ የሙከራ ቅጥር ሳይቆጠር፣ የጤና እና የፖሊስ ማስረጃ ሳይጠየቅ፣ ሌሎች በአዋጁ የተቀመጡ መብቶች እና ጥቅሞች ተጠብቀውለት በዝውውር እንዲስተናገድ የሚገልፅ አሰራር ተካቷል።

በተለያየ የስራ ቦታ የሚገኙ ባለትዳሮችን ለማገናኘት ሲባል የመንግስት ሰራተኛውን ስምምነትን መሰረት በማድረግ ተመሳሳይ መደብ ካልተገኘም ዝቅ ባለ ደረጃ እና ደመወዝ አዛውሮ ማሰራት እንደሚቻልም በረቂቁ ላይ ቀርቧል።

ፈቃድን በተመለከተ ለሴት የመንግስት ሰራተኞች የሚሰጠው የድህረ ወሊድ ፈቃድ ከ60 ቀናት ወደ 90 ቀናት ከፍ እንዲል ተደርጓል።

ይህም የሆነው እናቶች ህጻኑን ለመንከባከብ በቂ የእረፍት ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች አስተያየት በመስጠታቸው እና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ነው።

የወሊድ ፈቃድ ድንጋጌው ፅንስ የተቋረጠባቸው ሴቶችን ያካተተ ሲሆን፥ በተለይም የቅድመ ወሊድ ከወሰዱ በኋላ የፅንስ መቋረጥ የሚያጋጥማቸው ሴቶች የመውለጃ ወራቸው ከገባ በኋላ በመሆኑ የፅንስ መቋረጥ ያጋጠመበትን ጊዜ መሰረት በማድረግ የቅድም ወሊድ ወይም የድህረ ወሊድ ፈቃድ የምትተቀምበት አሰራር እንዲካተት ተደርጓል።

ባል የትዳር አጋሩ ስትወልድ 5 ቀን ብቻ ፈቃድ እንዲሰጠው ማድረጉ በቂ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ስለሆነ ወንዶች የአጋርነታቸውን ሚና እንዲጫወቱ 10 ቀናት እንዲሰጣቸው በሚል ተሻሽሏል።

የህመም ፈቃድን በተመለከተ አሁን ስራ ላይ ያለው አዋጅ በዓመት ፈቃድ ላይ ያለ ሰራተኛ ስትታመም በምን መልኩ እንደሚስተናገድ በግልፅ አላስቀመጠም።

ይህ ደግሞ ችግር ስላስከተለ በዓመት ፈቃድ ላይ የሚገኝ ሰራተኛ ከታመመ እና በሃኪም ፈቃድ ከተሰጠው የዓመት ፈቃዱ ተቋርጦ የህመም ፈቃዱን እንዲጠቅም እንደሚደረግ በግልፅ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል የህመም ፈቃድ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከሙሉ ደመወዝ ጋር፣ ለተከታዮቹ ሶስተ ወራት ደግሞ ከግማሽ ደመወዝ ጋር እና ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ያለደመወዝ እንደሚሰጥ ነባሩ አዋጅ ይደነግጋል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከሙሉ ደመወዝ ጋር፣ ለተከታዮቹ ሁለት ወራት ደግሞ ከግማሽ ደመወዝ ጋር እንዲሰጣቸው በሚል ተሻሽሏል።

በአዋጁ ላይ ሌሎች በርካታ ማሻሻያዎችን ያካተተ ሲሆን፥ የምክር ቤቱ አባላት ከመረመሩት በኋላ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

 

 

 

 

በምህረት አንዱዓለም