የፍልስጤሙ መሪ መሀሙድ አባስ በ10 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዛን ሊጎበኙ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የፍልስጤሙ መሪ መሀሙድ አባስ በ10 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያቸው የሆነውን ጉብኝት በጋዛ ሰርጥ ሊያደርጉ ነው።

የአባስ ጉብኝት ይፋ የሆነው ፋታህ እና ሀማስ ለዓመታት የኖረውን ልዩነታቸውን ለማስታረቅ በግብፅ አደራዳሪነት መስማማታቸው ከተነገረ ከሰዓታት በኋላ ነው።

በጋዛ ከፍተኛው የፋታህ መሪ ዘካሪያ አል አግሃ፥ አባስ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጋዛ ሰርጥን ይጎበኛሉ ብለዋል።

ሃማስ የአባስን ፋታህ ከጋዛ ሰርጥ በፈረንጆቹ 2007 ካስወጣ በኋላ መሀሙድ አባስ አከባቢውን ጎብኝተው አያውቁም።

ባሳለፍነው ወር ሃማስ ጋዛን የሚያስተዳድረውን ኮሚቴውን ለመበተን መስማማቱ የሚታወስ ሲሆን፥ ይህ ውሳኔ የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር እና የፋታህ መሪው የማህሙድ አባስ ፍላጎት ነበር ።

በስምምነቱ መሰረትም የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ራሚ ሃምዳላህ ጋዛን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

ምንጭ፦ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን.