የከተሞችን ወቅታዊ ሁኔታ ያካተተ የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተሞችን ወቅታዊ ሁኔታ ያካተተ የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም ለምክር ቤቱ አባላት የአዋጁን አስፈላጊነት እና ይዘቱን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የከተሞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣት ከተሞችን ለመምራትና ለማስተሳሰር የሚያስችል ፕላን ማስፈለጉ ለረቂቅ አዋጁ መውጣት ምክንያት ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ሲሰራበት የነበረው አዋጅ ቁጥር 574/2000 በአፈጻጸም ረገድ ችግሮች ይታዩበት ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ የነባሩን አዋጅ ክፍተቶች ለማስተካከል እና ተጨማሪ አሰራሮችን ማከል በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁተዘጋጅቷል።

አዳዲስ የፕላን ዓይነቶችን ለማካተት፣ የህብረተሰቡን እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ባለቤትነት አጉልቶ ለማሳየት፣ የፕላን ጥሰት የሚፈፅሙትን በህግ ተጠያቂ ማድረግ ማስፈለጉም የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጁ እንዲዘጋጅ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል።

የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጁ ያካተታቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በተመለከተም አቶ አማኑኤል ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በረቂቅ አዋጁ የከተሞች ወሰን፣ መሰረታዊ ካርታ፣ ሀገራዊ የከተማ ልማት ፕላን፣ ክልላዊ የከተማ ልማት ፕላን፣ ከተማ አቀፍ ፕላን እና ዝርዝር የማስፈፀሚያ ፕላኖች እንዲሁም ስኬች ፕላን በረቂቅ አዋጁ በዝርዝር ቀርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ረቂቅ አዋጁ ፕላን ስለማመንጨት እና ስለማዘጋጀት፣ ፕላን ስለማፅደቅ፣ የፀደቁ ፕላኖችን ስለማስተዋወቅና ቅጅ ስለመስጠት፣ ፕላኖችን ስለመተግበር፣ ፕላኖችን ስለመከለስ እና ስለማስተካከል ዝርዝር ጉዳዮች ይዟል።

በምክር ቤቱ አባላት የተመረመረው ረቂቅ አዋጁ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የተመራ ሲሆን፥ ፀድቆ ወደ ተግባር ሲገባ ከተሞች ተመጋጋቢና ዘመናዊ የአከታተም ስርዓትን እንዲከተሉ ያስችላቸዋል ተብሏል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው የ3ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባው፥ ከከተሞች ፕላን ረቂቅ አዋጅ ውጭ ሌሎች ሰባት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

ምክር ቤቱ የቤተሰብ ህግን ስለማሻሻል፣ ስለኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ምዝገባ እና አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበረን እንድገና ለማቋቋም የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሯል።

ከዚህም በተጨማሪ የማሪታይም አሰሪና ሰራተኛ ኮንቬንሽን፣ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራትን ዓለም አቀፍ ሀሳብ አመንጪ መመስረቻ ባለብዙ ወገን ስምምነት፣ የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ስምምንትን፣ የፌደራል መንግስት ሰራተኞችን በተመለከተ ተዘጋጅተው የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን ነው መርምሮ ለቋሚ ኮሚቴዎቹ የመራው።

 

 

በንብረቴ ተሆነ