የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መዳከም በምሁራን ዓይን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ጀምሮ የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲዳከም መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።

የብር የውጭ ምንዛሬ እንዲዳከም የተወሰነው ውሳኔ ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ሊያሳድግላት እንደሚችል ነው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

ሆኖም መንግስት ይህንን ተከትሎ ሊመጣ የሚችል የዋጋ ግሽበትን በተገቢው መንገድ ሊከላከል እንደሚገባም ምሁራኑ አሳስበዋል ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፥ የአንድ ሀገር ገንዘብ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ያለው ዋጋ ሲዳከም የወጪ ንግዷ ይነቃቃል።

የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በተለይ ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ያለው ዋጋ በአንጻሩ ጠንካራ ነው።

ይህም ማለት ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ባለሀብቶች ያመጡት ምንዛሬ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር አነስተኛ ሆኖ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሀና እንደሚሉት የምንዛሬ ተመን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ላኪዎችን የሚያበረታታ አይደለም።

ላኪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑት ደንበኛ የሆኑበት ባንክ ምርት ወደ ውጭ ልከው ካመጡት ምንዛሬ የተወሰነው እንዲሰጣቸው በመስማማት አትራፊ የሚያደርጓቸውን ምርቶች ከሌሎች ሀገራት በማምጣት ኪሳራቸውን ስልሚያካክሱት ነው ብለዋል።

ሌላኛው የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ደግሞ ከቡና አንጻር ያለውን በምሳሌነት ያነሳሉ።

ቡና አገር ውስጥ በውድ ዋጋ እንደሚሸጥ የሚያነሱት ምሁሩ፥ የብር የምንዛሪ ተመን በዚህ መልኩ መስተካከሉ ግን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ የውጭ ምንዛሪ እንዲያመጣ ያበረታታል ነው ያሉት።

በዚህም መሰረት ዛሬ አንድ የአሜሪካ ዶላር ላመጣ ሰው 23 ብር የሚሰጠው ከሆነ በአንፃሩ በሌላ ጊዜ የብር መጠኑ ወደ 26 ቢጨምር ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ፍላጎቱ ከፍ ይላል ማለት ነው።

በሌላ በኩል የብር የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ከሌሎች ሀገራት ገንዘብ አንጻር እንዲዳከም ማድረጉ፥ ኢትዮጵያ ታዳጊ ሀገር በመሆኗ ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ እቃዎችን ከውጭ ለማስገባት ፈተና አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው፥ በሀገሪቱ ከኢንቨስትመንት የሚገኝ ትርፍ ከበርካታ ሀገራት አንጻር ከፍተኛ ነው ይላሉ።

ይህ ደግም አንድ ባለሀብት የኢንቨስትመንት ጥሬ እቃ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚጠየቀው ገንዘብ ቢጨምርም፥ ከሚያገኘው ትርፍ አንጻር አሁንም አነስተኛ ስለሚሆን የብር የውጭ ምንዛሬ ተመኑ መዳከሙ ተጽእኖው ያን ያህል ነው ብለዋል።

መንግስት የሚያከናውናቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ተጽእኖ አይኖረውም በሚል ለተነሳው ጥያቄ፥ እነዚህ ፕሮጀክቶች አሁንም የሚያስገኙት ጥቅም ዛሬ ካለው የምንዛሬ ለውጥ ስለማይብስ እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ በተወሰነ መልኩ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያስከትል ነው ያነሱት።

ይኸውም ለምሳሌ ዶላርን ለመግዛት ዋጋው ከአሁኑ ከፍ ያለ ብርን ስለሚጠይቅ ሀገር ወስጥ የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ ሊያስወድድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሆኖም መንግስት የምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ተከተትሎ የሚመጣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መዘጋጀት እንዳለበት ምሁራኑ ተናግረዋል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ከፍተኛ ዋጋ ጭማሬን ሊያደርጉ የሚችሉ ነጋዴዎችን ከመቆጣጠር ባለፈ መጠነኛ የሆነ የዋጋ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት ።

ፕሮፌሰር ጣሰው ደግሞ የግብር አሰባሰቡ ላይ ከፍተኛ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያውን ተከትሎ የቀን ተቀን መጠቀሚያ ምርቶች ሊወደዱ ስለሚችሉ በተለይ በደሞዝ በሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫናን ሊፈጥር እንደሚችል ተጠቁሟል።

በመሆኑም መንግስት ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ምርቶችን እያቀረበ ዋጋን የማረጋጋት ስራው ላይ ጠንካራ መሆን እንዳለበት እና እንደ “አለ በጅምላ” ያሉ ተቋማት ሊጠናከሩ እንደሚገባቸው ይነሳል።

ምሁራኑ በምንዛሬ ተመን ማስተካከያው ሊፈጠር የሚችል ግሽበት የአንድ ጊዜ እንጂ፥ ያን ያህል ጠቅላላ ኢኮኖሚውን የሚጎዳ አይደለም ብለዋል፤ ይህንን ሀሳብ የብሔራዊ ባንኩ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ ይጋራሉ።

የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጡ ከረጅም ጊዜ አንጻር ከታየ ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ፕሮፈሰር ጣሰው ያነሱ ሲሆን፥ ማስተካከያው የወጪ ንግድ ገቢን እንደሚያሳድግ፣ ምርቶችን ሀገር ውስጥ ለማስገባት ምንዛሬ የማግኘት አቅምን ይጨምራል ነው ያሉት።

ይህ ካልሆነ አሁን እየተሰሩ ያሉ መሰረተ ልማቶችን እየተገነቡ የሚቀጥሉት የምንገዛውን ከምንሸጠው በጣም እያሳነስን ይሆናል፤ ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት ምጣኔ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ ምርቶችን አስቀድሞ ለማወቅ እና ለጥንቃቄ ያግዛል ነው ያሉት ፕሮፈሰር ጣሰው።

ይህም ማለት ከውጭ ከሚገቡ ሸቀጦች መካከል እጀግ አስፈላጊ የሆኑትን ብቻ እንድንመርጥ ያደርጋል ባይ ናቸው።

ከዚህ ውጭ ገንዘብን ከሌሎች ሀገራት ምንዛሬ አንጻር አዳክሞ የወጪ ንግድን ማሳደግ አዲስ ነገር አይደለም ይላሉ።

በተለይ እንደ ቻይና ያሉ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ተመሳሳይ ነገርን በማድረግ የወጪ ንግድ ገቢያቸውንና ተወዳዳሪነቱን ማሳደጋቸውን ፕሮፈሰር ጣሰው በማሳየነት አንስተዋል።

ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው የ15 በመቶ የተመን ማስተካከያ ተመሳሳይ ውጤትን ለኢትየጵያ እንደሚያመጣ እና የጥቁር ገበያውን እንቀስቃሴ ለማዳከም ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል።

ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አካላት አሉ።

በዛሬ የምንዛሬ ተመን የውጭ ምንዛሬ ገዝቶ ያከማቸ ባንክ፥ ነገ ዋጋው ከፍ ስለሚል የሚያገኘው ትርፍ በንፋስ አመጣሽ ትርፍ የሚወሰድ ነው።

የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ባወጣው የታክስ ህግ ደግሞ ከዚህ ትርፍ ላይ ግብር የመጣል ስልጣን አለው።

ለምሳሌ የዛሬ ሰባት ዓመት ብር በ22 በመቶ አካባቢ እንዲዳከም ሲደረግ፥ ከዚህ ተጠቃሚ የሆኑ ባንኮች ከትርፋቸው 70 በመቶ ግብር እንዲከፍሉ የሚያደርግ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ ሆኖ ነበር።

ይህ የሚደረገው ባንኮቹ ትርፉን ያገኙት መንግስት ባወጣው ህግ ስለሆነ ትርፉ ወደ መንግስት ማድላት ስላለበት ነው።

አሁንም በዚህ የምንዛሬ ለወጥ ምክንያት ንፋስ አመጣሽ ትርፍ የሚያገኙ ባንኮች የትርፋቸው ሁኔታ ገቢያቸው ታይቶ ግብር እንዲከፍሉ የሚደረግ ይሆናል።

 

 

 

 በካሳዬ ወልዴ