የሀገሪቱን የአየር ትንበያ አቅም የሚያሳድግ ዘመናዊ ራዳር ሊተከል ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 4 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ እንዳለው ራዳሩ 4 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ፥ የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽል ታምኖበታል።

የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ለትንበያ የሚያገለግሉትን የመረጃ ግብዓት መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን  ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው የሚናገረው።

ከእነዚህ ዘመናዊ መሳሪያዎች ወስጥ አንዱና ዋነኛው ደግሞ በጣና በለስ ፕሮጀክት  ከአለም ባንክ  በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተገዛው ዘመናዊ ራዳር ነው።

ራዳሩ የ4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የወጣበት ሲሆን ፥ መረጃዎችን በስፋትና በፍጥነት ለመሰብሰብ የሚያስችል ነው።

ራዳሩ በግብርናው ዘርፍም በእርሻና በሰብል መሰብሰቢያ  ወቅቶች  የሚፈጠሩ ድንገተኛ የጎርፍ ክስተቶችንና የዝናብ መዛባትን ለአርሶ አደሩ በፍጥነት ለማሳወቅ እንደሚረዳ ነው የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም የሚናገሩት።

ይበልጥ ደግሞ በሀገሪቱ በመከናወን ላይ ላሉ ሰፋፊ የእርሻ ፕሮጀክቶች ህልውና መሳሪያው በመሆን ፥ የእርሻ ፕሮጀክቶቹን ከድንገተኛ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል የሚኖረው ሚናም የጎላ ነው ያሉት።

መሳሪያው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ሻውራ አከባቢ የሚተከል ሲሆን ፥ በቀጣይም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጨማሪ ራዳሮችን ለመትከል ማቀዱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በራዳሮቹ የሚገኘውን መረጃ የሚቀበሉ ከመቶ በላይ ተጨማሪ የአውቶማቲክ የአየር ትንበያ ጣቢያዎችም በግንባታ ላይ እንደሚገኙና እነዚህ ጣቢያዎችም በየ15 ደቂቃው መረጃዎችን እየተቀበሉ ወደ ዋናው ማእከል እንደሚልኩ አቶ አህመዲን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በጤና፤ በትራንስፖርትና በግብርናው ዘርፍ የሚከሰቱ ድንገተኛ ጉዳቶችንና ክስረቶችን በሚገኘው ቅድመ ትንበያ መሰረት ለመከላከል ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው የታመነበት ይህ ራዳር በመጪው አመት ስራ እንደሚጀምር ኤጀንሲው ገልጿል ።

በአብነት ታምራት