ለሮሂንጊያዎች እርዳታ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በትንሹ 9 ሰዎች ሞቱ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ባንግላዲሽ ውስጥ ለሮሂንጊያ ስደተኞች እርዳታ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በትንሹ 9 ሰዎች ሞቱ።

ተሽከርካሪው እርዳታውን ጭኖ በዳገታማ መንገድ ሲጓዝ የመንሸራተት አደጋ አጋጥሞታል።

በአካባቢው በሚገኝ የሩዝ ማሳ ተገልብጦ በትንሹ ዘጠኝ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ፥ 10 ሰዎች መጎዳታቸውን ፖሊስ እና የእርዳታ ሰራተኞች ተናግረዋል።

አደጋው በበርማ ድንበር አቅራቢያ የሮሂንጊያ ስደተኞች በሰፈሩበት የባንግላዲሽ አካባቢ ነው የደረሰው።

ሮሂንጊያዎች ካሳለፍነው የነሃሴ ወር ጀምሮ በማይናማር እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት ለመሸሽ ወደ ባንገላዲሽ እየተመሙ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሮሂንጊያ ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ የማይናማር ወታደሮች ያደረሱትን ጥቃት በዘር ማጥፋት የሚፈረጅ ነው ማለቱ አይዘነጋም።

ዛሬ በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ ከሞቱት መካከል ስድስቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ፥ ሶስቱ ወደ ሆስፒታል እየተወሰዱ በነበረበት ወቅት መንገድ ላይ ህይወታቸው ማለፉን የአካባቢው የቀይ ጨረቃ ማህበር ባለስልጣን ኤ.ኬ.ኤም ጃሃንጊር ተናግረዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ጉዳት የደረሰባቸውና ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች የቀን ሰራተኞች ሲሆኑ፥ ተሽከርካሪው የጫነውን የእርዳታ አቅርቦት ለሮሂንጊያዎች ለማሰራጨት እንዲያግዙ አብረው ሲጓዙ የነበሩ ናቸው።

አሁን ከማይናማር ፈልሰው ወደ ባንግላዲሽ የገቡት ሮሂንጊያዎች ቁጥራቸው 422 ሺህ ደርሷል።

 

 

 

 


ምንጭ፦ሬውተርስ