የግል የንግድ ድርጅቶች ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያግዝ ስርዓት ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግል የንግድ ድርጅቶች ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያግዝ አዲስ ስርዓት ሊዘረጋ ነው። 

ስርዓቱ የግል ባለሃብቶች በተናጥል የሚያድርጉት ማህበራዊ ድጋፍ የተቀናጀና ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያድረግ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት በሚዘረጋው አዲስ ስርዓት ላይ ከግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት ተደርጎበታል።

ሊዘረጋ ይገባል ተብሎ ውይይት የተደረገበት ሰነድ የግሉ ባለሃብት ድጋፍ በተቀናጀ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ በማሳተፍ ሁሉንም የግል ባለሃብት አሳታፊ በሆነ መልኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፥ አሰራሩ ባደጉት ሃገራት የተለመደ እና አስተዋፅኦውም የተሻለ መሆኑን ገልጿል።

በሃገራችን ግን እስካሁን በተናጠል የሚደረግ ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር በተቀናጀ መልኩ ድጋፍን ለማካሄድ የሚያስችል አሰራር አለመኖሩ ተጠቁሟል።

ዓላማውም ፈንድን በማቋቋም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም የግል ባለ ሃብት በየዓመቱ ከሚያገኙት ትርፍ ላይ ወደ ፊት በሚስማሙበት መጠን ወደ ቋቱ በማስገባት ችግሩ ሲፈጠር ወይም ለግሉ ባለ ሃብት ድጋፍ ሲፈለግ በቀላሉ ከቋቱ በማውጣት ድጋፉን ማድረግ እንዲቻል ነው ተብሏል።

በመሆኑም ቀደም ሲል በተወሰኑ ባለ ሃብቶች ላይ ብቻ ጫናው ያርፍ የነበረው የድጋፍ ጥሪ ሁሉም ባለ ሃብት በአቅሙ እንዲደርሰው እና ሃላፊነቱንም እንዲወጣ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።

የሚቋቋመው ፈንድ ለድጋፍ ጥሪ ምላሽ ከመስጠት ባሻገርም በርካታ ሃላፊነቶች ይኖሩታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የሚፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም፣ ለወጣቱ ትውልድ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ የምርምር እና የልማት ስራዎችን መደገፍ፣ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችንና ዘመናዊ የግብርና ስራዎችን እንዲስፋፉ መደገፍ፣ የአካባቢ ብክለትን መከላከል እና ለወጣቶች የስልጠና ድጋፎችን መስጠት የሚሉት ዋና ዋና ተግባራት ናቸው።

በተጨማሪም የድንገተኛ እና የአስቸኳይ እርዳታዎችን ጨምሮ ለልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳቶች አፋጣኝ ምላሾችን ይሰጣል፤ እንዲሁም ከአከባቢው አጠቃላይ የልማት ዕድገት ጋር ተያይዞ ለዕቅዶች እና እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት አስፈላጊ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።

ዛሬ ይህንን ፈንድ ለማቋቋም በሚያስችል ውይይት የተደረገበት ሰነድ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ተቀይሮ የንግዱ ዘርፍ ተወካዮች በተገኙበት የምስረታ ጉባኤው እንዲካሄድ መወሰኑ ተገልጿል።

 

በትዕግስት ስለሺ