የአዲስ ፕሪፋብ አክሲዮን ማህበርና የሆሴ ሪል ስቴትን ውዝግብ ውስጥ የከተተው መሬት ጉዳይ እልባት ሳያገኝ 2 ዓመት አልፎታል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ ፕሪፋብ አክሲዮን ማህበርና የሆሴ ሪል ስቴትን ውዝግብ ውስጥ የከተተው መሬት ጉዳይ እልባት ሳያገኝ 2 ዓመት ከ6 ወር አልፎታል።

አዲስ ፕሪፋብ አክሲዮን ማህበር 861 አባላትን ይዞ በ37 ሚሊየን ብር መነሻ ካፒታል በዘመናዊ ተገጣጣሚ ቤት አምራች ኢንዱስትሪነት የምዝገባ ፈቃድ አውጥቶ በ2004 ተመሰረተ።

መስራች አባላቱ የአክሲዮን ማህበሩ ባለድርሻ ከመሆናቸውም ባሻገር የሚገጣጠሙ ቤቶችን የማግኘት የቅድሚያ እድል እድል እንደሚሰጣቸው በወቅቱ የነበሩት የአክሲዮን ማህበሩ አመራሮች ነግረዋቸዋል።

ይህን መሰረት በማድረግም የማህበሩን ቤት ለማግኘት ጉጉት ያደረባቸው ከ500 በላይ የማህበሩ አባላት ተገጣጣሚ ቤቶቹን ለማግኘት ይመዘገባሉ።

በመሃል ግን ቤት ተመዝጋቢዎቹን ጨምሮ በማህበሩ አባላትና አመራሮች የቤቶቹ የግንባታ ፍጥነትና የማህበሩ የፋይናንስ አወጣጥ ላይ አለመግባባትይፈጠርና የቀድሞ አመራሮችን በማውረድ ሌላ አዲስ የቦርድ አመራሮች ተመርጠው ተሾሙ።

እነዚህ የተመረጡት የቦርድ አመራሮች የማህበሩን ሃብት ማሰባሰብ የመጀመሪያ ስራቸው አድርገው ጀመሩ።

ተገጣጣሚ ቤቶቹ የሚገነቡበት በቦሌ በሻሌ 49 ማዞሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ 23 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ነው።

የዚህ መሬት የሊዝ ጊዜው ማብቂያው በመቃረቡ እድሳት ስለሚያስፈልገው፥ የቦርዱን ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስን ጨምሮ ሌሎች አመራሮቹ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሂደው የመሬት ሊዝ እድሳት ይጠይቃሉ።

ፅህፈት ቤቱ የሰጣቸው ምላሽ ግን የመሬቱ ካርታ መክኗል የሚል ነበር።

በዚህ ሁኔታ አክሲዮን ማህበሩ ከሌላ የሪል ስቴት አልሚ ተቋም ጋር ሌላ ውዝግብ ውስጥ ገባ።

ካርታው መክኗል የተባሉበትና የአዲስ ፕሪፋብ አክሲዮን ማህበር ጅምር ተገጣጣሚ ቤቶች ያረፈበት 23 ሺህ ካሬ ሜትር የቦሌ በሻሌ መሬት ንብረትነቱ መጀመሪያ ሆሴ ሪል ስቴት ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚባል ነበር።

አዲስ ፕሪፋብ አክሲዮን ማህበር ደግሞ ከዚህ ሪል ስቴት ጋር በታህሳስ 13 ቀን 2005 ዓ.ም በገባው ስምምነት ሪል ስቴት በጋራ ለማልማት የሚል “የእሽሙር ሽርክና” አለው።

ይህ የእሽሙር ሽርክና ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ሁኖ በታህሳስ 13 ቀን 2007ዓ.ም ያበቃ ነበር።

ከስምምነቱ በኋላ ሆሴ ሪል ስቴት የ23 ሺህ ካሬ ሜትር ሙሉ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶቹን በሙሉ ለአዲስ ፕሪፋብ አስረክቦ ዞር አለ።

በመሃል ሃምሌ 30 ቀን 2006 ላይ ሆሴ ሪል ስቴት ከአዲስ ፕሪፋብ ጋር የገባውን የሁለት ዓመት የሽርክና ስምምነት በመጣስ፥ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ካርታየ ጠፋብኝ የሚል ማስታወቂያ በማስነገር በምትኩ ሌላ ካርታ እንዳስወጣ እነ አቶ ቴዎድሮስ ይደርሱበታል።

ሆሴ ይህን ማስታወቂያ ያስወጣው ታዲያ ካርታው በማን ስር እንደሚገኝ እያወቀ ነው።

ውዝግቡም በዚህ የጀመረ ሲሆን እነ አቶ ቴዎድሮስ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ድረስ ቅሬታቸውን አቀረቡ።

በቃል አስተያየታቸውን ለመስጠት ያልፈለጉት የሆሴ ሪል ስቴት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ የማነ ገብረስላሴ በጠበቃቸው በኩል ላፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በፅሁፍ ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም “በእሽሙር ሽርክናው መሰረት ማህበሩ ቤቶቹን ሰርቶ ለተጠቃሚዎች ማስረከብ መቸገሩንና የማህበሩ አመራሮች ከአባላቱ ጋር ውዝግብ ወስጥ መግባቱ ሽርክናውን አደጋ ውስጥ እንዳስገባው ጠቅሰዋል።

“የማህበሩን አመራሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ሞክሬ ላገኛቸው ስላልቻልኩ፥ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ የካርታ ጠፋብኝ ማስታወቂያ ባስወጣም አቤት ባይ ባለመገኘቱ አዲስ ካርታ በማስወጣት ቦታውን አስከብሪያለሁ” ነው ያሉት።

በአቶ ቴዎድሮስ የሚመራው አዲሱ የአዲስ ፕሪፋብ አክሲዮን ማህበር አመራር ግን ቦታው ለእኛ ነው የሚገባ ይላል።

የባለቤትነት ማስረጃቸው ደግሞ ቦታው በእሽሙር ሽርክና ስም ለማህበሩ የተሸጠ ነው የሚል ነው።

የእሽሙር ሸርክናው በመንግስትና በማህበሩ አባላት እንዳይታወቅ ስምምነቱ በሶስተኛ ወገን መታወቅ የለበትም የሚል ድንጋጌ፥ በውሉ ውስጥ መግባቱ ራሱ የቀድሞ የማህበሩ አመራሮችና ሆሴ መሬቱን በድብቅ እንደተሻሻጡ ማረጋገጫ መሆኑን ያነሳሉ።

እነ አቶ ቴዎድሮስ ሆሴ ሪል ስቴትና አዲስ ፕሪፋብ የእሽሙር ሽርክና በፈፀሙበት ተመሳሳይ ዕለት በታህሳስ 13 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ ፕሪፋብ ከሆሴ ሪል ስቴት ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ የማነ ገብረስላሴ ጋር የብድር ውል ስምምነት መፈፀማቸውን መሬቱ እንደተሸጠልን የሚያረጋግጥ ነው በሚል በማስረጃነት አቅርበውታል ።

የብድር የውል ስምምነቱ በወቅቱ ሆሴ ሪል ስቴት መሬቱን ለማህበሩ ለመሸጥ የሊዝ ህጉ ስለማይፈቅድለት በብድር ሽፋን ለሆሴ 20 ሚሊየን ብር ስለመከፈሉ የሚያረጋግጥ የባንክ ቼኮች በማስረጃነት አቅርበዋል።

የሆሴ ሪል ስቴት ባለቤት አቶ የማነ ግነ ይህን የብድር ውል ሆሴ አያውቀውም፤ የብድር ውልም ከአዲስ ፕሪፋብ ጋር የለውም ሲሉ በፅሁፍ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

እነ አቶ ቴዎደሮስ ግን የማህበራቸው የቀድሞ የቦርድ አመራሮች የስብሰባ ቃለ ጉባኤዎችና ሪፖርቶችን በመጥቀስ ቦታው በማህበሩ እንደተገዛ የሚናገሩ እንደሆነ በሰነድ ጭምር ይሞግታሉ።

ከየካቲት 2 እስከ 9 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ የማህበሩ የቦርድ አመራሮች የተሰበሰቡበት ቃለ ጉባኤ እንደሚያሳየው፥ መሬቱ በእርግጥም ለአክሲዮን ማህበሩ የተሸጠ ያመላክታል።

አሁን ላይ አዲስ ፕሪፋብ አክሲዮን ማህበርና ሆሴ ሪል ስቴት የሚወዛገቡበትን ቦታ በየራሳቸው ጥበቃ ቀጥረው እያስጠበቁት ይገኛሉ።

አወዛጋቢውን ቦታ በተመለከተ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ የሚጠበቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ጉዳዩን እጁ ወስጥ ካስገባው ከሶሰት ወራት በላይ ተቆጥሯል።

የከንቲባ ፅህፈት ቤት ሀላፊው አቶ አሰግድ በስልክ በሰጡት ቃል፥ ምናልባት በዚህ ሳምንት አልያም በቀጣይ ሳምንት ካቢኔው በጉዳዩ ላይ መክሮ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ ተናግረዋል።

 


በታደሰ ብዙዓለም