የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀመረ።

እስከ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሚቆየው ስብሰባ ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴው በ2009 በጀት ዓመት ዋና ዋና የልማትና የድርጅት ሥራዎች ላይ በመምከር ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የማዕከላዊ ኮሚቴው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮነን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፥ ኮሚቴው በአራት አጀንዳዎች ላይ ተመስርቶ ውይይት ያካሂዳል።

በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ድርጅቱ በየደረጃው ያካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ እንዴት እንደተመራ፣ የመጡ ለውጦችና ቀሪ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔ ያሳልፋል።

ሕብረተሰቡ ያነሳቸው አንገብጋቢ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከተሃድሶ ንቅናቄው ማግስት ጀምሮ እየተፈቱ የመጡበትን አግባብንም ማዕከላዊ ኮሚቴው ይገመግማል።

መደበኛ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ዕቅድ አፈጻጸምም ላይ ውይይት በማደረግ ጠንካራ አፈጻጸሞች የቀጣይ ዕቅድ አካል ሆነው እንዲቀጥሉ እና የተስተዋሉ ክፍተቶችም የሚታረሙበት አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

አቶ አለምነው እንዳሉት፥ በቀጣዩ መጋቢት ወር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን 12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ በስኬት ለማከናወን ከወዲሁ የአዘጋጅ ኮሚቴ በሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴው እንደሚወያይም አመልክተዋል።

የ2009 በጀት ዓመት የድርጅቱ ገቢና ወጪ ሪፖርት ለማዕከላዊ ኮሚቴው ቀርቦ ውይይት የሚካሄድበት ከመሆኑ በተጨማሪ በሂስና ግለ ሂስ የታገዘ የአመራሩ የአካል ግምገማ እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

በመጨረሻም ማዕከላዊ ኮሚቴው የ2010 በጀት ዓመት መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራ ዕቅድ ላይ በሰፊው በመምከር በላቀ ጥራትና ውጤታማነት የሚፈጸምበትን አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም "ተግባራዊ ለውጥና ውጤታማነት" በሚል መሪ ቃል ላይ ተመስርቶ የሕዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እንደሚከናወንም አቶ አለምነው ገልጸዋል ።

ምንጭ፦ ኢዜአ