በአሜሪካ ዴሞክራቶች ከትራምፕ ጋር በሰነድ አልባ ወጣት ስደተኞች የመስራትና የመማር መብት ዙሪያ መስማማታቸውን እየገለፁ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዩናይትድ ስቴትስ በኮንግረሱ የዴሞክራቶች መሪዎች ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም ጋር በህፃንነት የእድሜ ክልል ወደ አገሪቱ መጥተው መኖር የጀመሩ ሰነድ አልባ ወጣት ስደተኞችን በጊዜያዊነት የመስራት እና የመማር መብት ለመጠበቅ የሚያስችል ስምምነት መድረሳቸውን ገለፁ።

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን የወጣው ህግ በታዳጊነት እድሜያቸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ሰነድ አልባ ወጣት ስደተኞች በዚያች አገር እንዲሰሩ እና እንዲማሩ ጊዜያዊ መብት የሚሰጥ ነበር።

ይህ 800 ሺህ ወጣት ስደተኞች ከመባረር ተጠቃሚ ያደረገውን ህግ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚሽሩት በመግለፅ፥ ኮንግረሱ ይህን የሚተካ ሌላ ህግ እንዲያረቅ ጠይቀው ነበር።

ሆኖም ትናንት በዋይት ሀውስ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለእራት በአንድ ጠረጴዛ የተቀመጡት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራቶች መሪ የሆኑት ናንሲ ፔሎሲ እና በሴኔቱ አናሳ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች ስብስብ መሪ የሆኑት ቻክ ስኩነር የእነዚህን ወጣቶች መብት በሚያስጠብቅ ህግ ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን ነው የተናገሩት።

ስምምንቱን አስመልክቶ ትራምፕ ምናልባትም ከወግ አጥባቂ ደጋፊዎቻቸው ተቃውሞ ሊገጥማቸው ይችላል።

ፖለቲከኞቹ በውይይታቸው ከዚህ ህግ በተጨማሪ የታክስ ማሻሻያ እና የድንበር ፀጥታ ጉዳይ አጀንዳዎች ነበሩ።

ምንጭ፦ ዘ ጋርድያን