በኢትዮጵያ የአፍሪካ ልማት ባንክ በፋይናንስ የደገፋቸው ፕሮጀክቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ተፅእኖ እየፈጠሩ ነው - ባንኩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች በአገሪቱ የማህበረ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አወንታዊ ተፅእኖ እየፈጠሩ መሆናቸውን መገንዘቡን ባንኩ ገለፀ።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የባንኩ የምስራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ካሌብ ዌጎሮ በጉብኝታቸው ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ባንኩ በፋይናንስ የደገፈውን የሀገረማርያም-ሞያሌ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የሚገኝበትን ደረጃ በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል።

በኢትዮጵያ በኩል 80 በመቶ እና በኬንያ በኩል ሙሉ በሙሉ ግንባታው የተጠናቀቀው ይህ መስመር የሁለቱን አገራት የንግድ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ነው የተናገሩት።

ሌላው ባንኩ በፋይናንስ የደገፈው የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ መስመር አካል የሆነው የሞጆ ዝዋይ መስመር ግንባታ 30 በመቶ መጠናቀቁን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በዚህ 100 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው ክፍል ላይ 1 ሚሊየን የዛፍ ችግኝን ለመትከል መታቀዱን አድንቀዋል።

ከኢትዮጵያ እስከ ኬንያ የሚዘልቀውና ባንኩ የ200 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ፋይናንስ ያቀረበለት 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከፍተኛ ቮልቴጅ ተሸካሚ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረዳታቸውን አንስተዋል።

ባንኩ በፋይናንስ የደገፋቸው የትራንስፖርት እና የሀይል ፕሮጀክቶች በአገሪቱ የማህበረ ኢኮኖሚ እድገትን ከማምጣት ባለፈ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር አጋዥ እንደሚሆኑ ነው ያነሱት።

በቆይታቸው ባንኩ ለኢትዮጵያ በቀጣይ ሊያቀርብ በሚችለው የፋይናንስ ድጋፍ ዙሪያ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም ተከስተ ጋር መወያየታቸውን ገልፀዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአውሮፓውያኑ 1975 ጀምሮ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

እስካሁን በትራንስፖርት፣ ሀይል፣ ግብርና እና ሌሎች ማህብራዊ ዘርፎች ላይ 4 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ፕሮጀክቶች በባንኩ የፋይናንስ ድጋፍ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ገብተዋል።

በአሁኑ ወቅትም 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ 22 ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በመከናወን ላይ ይገኛሉ።