የኢራቅ ፓርላማ የኩርዶችን የነፃነት ህዝበ ውሳኔ እቅድ ውድቅ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢራቅ ፓርላማ ኩርዶች ያቀረቡትን የራስ ገዝ አስተዳደርን የሚወስነውን የነፃነት ህዝበ ውሳኔ ውድቅ አደረገ።

ፓርላማው የባግዳድ መንግስት ከከፊል ራስ ገዝ የኩርዶች አስተዳደር ጋር እንዲስማማ ጥሪ አቅርቧል።

የኩርድ ግዛት አስተዳድር በመጪው የፈረንጆቹ መስከረም 25 ቀን የነጻነት ህዝበ ውሳኔ ሊያደርግ አቅዶ ነበር።

ሆኖም የኢራቅ ፓርላማ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ህዝበ ውሳኔው እንዳይካሄድ የተቃውሞ ውሳኔ አሳልፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አል አባዲ የኢራቅን አንድ የማድረግ ሃላፊነታቸውን ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ፓርላማው አሳስቧል።

በባግዳድና በኩርድ ዋና ከተማ ኤርቢል መካከል ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም ውይይት ሊጀመር እንደሚገባ ነው የገለፀው።

ከ328 የፓርላማ አባላት ውስጥ 204 በተገኙበት ስብሰባ የተላለፈው ውሳኔ የኩርድ ግዛትን የወከሉ አባላት አቋርጠው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።

ፈቃድ ያልተሰጠው የኩርድ የነፃነት የህዝበ ውሳኔ እቅድ በግዛቷ ነዋሪዎች መካሄዱ እንደማይቀር መረጃዎች እያመላከቱ ነው።

የኢራቅ መንግስት በበኩሉ ከአይኤስ ጋር የምናደርገውን እልህ አስጨራሽ ውጊያ ድል እንዳናደርግ እንቅፋት ከመሆንም ባለፈ በኢራቅ አለመረጋጋት እንዲያገረሽ ያደርጋል በሚል ህዝበ ውሳኔው እንዳይደረግ ተቃውሞውን አሰምቷል።

ቱርክ እና አሜሪካም የኢራቅን መንግስት አቋም ይጋራሉ።

ምንጭ፦ አናዶሉ