የቱርክ ፖሊስ 25 የአይኤስ ታጣቂዎችን ኢስታንቡል ውስጥ በቁጥጥር ስር አዋለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ ፖሊስ የአይኤስ አባል ናቸው በሚል የጠረጠራቸውን 25 ታጣቂዎች ኢስታንቡል ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።

ፖሊስ ታጣቂዎቹ በከተማዋ ጥቃት ለማድረስ አቅደው ነበር ብሏል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሶስቱ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸውን ጠቁሟል።

ፖሊስ 22 የሚሆኑት ታጣቂዎችም የውጭ ሀገር ዜግነት እንዳላቸው ነው የገለፀው።

ቱርክ ከዚህ በፊት ከአይኤስ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ከ5 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሏ ይታወቃል።

ለሽብር ቡድኑ ዓላማ ማስፈፀሚያ እያገለገሉ ነው ያለቻቸውን ከ95 ሀገራት የመጡ 3 ሺህ 290 የውጭ ዜጎችንም ከሀገሯ ማባረሯ ነው የተነገረው።

የአንካራ ባለስልጣናት ቱርክ ሽብርተኝነትን ለመከላከል 38 ሺህ 269 ሰዎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ መከልከሏን ጠቅሰዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት የቱርክ ፖሊስ በሜዲትራኒያን የባህር ዳርቻ በምትገኘው የሜርሲን ከተማ በአንድ የፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲያቀነባብር የነበረን አንድ የአይኤስ አባል መግደሉ ይታወሳል።

 

 

 

 

 


ምንጭ፦ሬውተርስ