በግብፅ በደረሰ የቦምብ ጥቃት የ9 ፖሊሶች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በግብፅ ሲናይ በረሃ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ዘጠኝ የፖሊስ አባላት ህይወት ማለፉ ተገለፀ።

በሰሜናዊ ሲናይ በረሃ በፖሊሶች ተሽከርካሪ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ህይወታቸው ካለፈው በተጨማሪም አራት የፖሊስ አባላቶች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።

አሸባሪው ኢስላሚክ ስቴት (አይ.ኤስ) ጥቃቱን እኔ ነኝ የፈፀምኩት ሲልም ሀላፊነቱም መውሰዱን አማቅ የተባለው የዜና አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል።

የሰሜን ሲናይ ግዛት አሪሽ ከተማ አቅራቢያ በተፈፀመው የቦምብ ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው የፖሊስ አባላት ውስጥ አንድ ብርጋዴር ጀነራል የሚገኙበት ሲሆን፥ በጥቃቱም አንድ እግራቸውን አጥተዋል ነው የተባለው።

በተጨማሪም ሶስት የጦር ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውም ተነግሯል።

ጥቃቱን ተከትሎም የግብፅ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር እስካሁን ስለጥቃቱ የሰጠው አስተያየት የለም ተብሏል።

ሜና የተባለው የሀገሪቱ የዜና ኤጀንሲ ግን ከፍተኛ የመንግስ ባለስልጣን ጥቃቱ መድረሱን እንዳረጋገጡለት አስታውቋል።

የቦምብ ጥቃቱ በተፈፀመበት ስፍራም የፀጥታ ሀይሎች ከጥቃቱ ፈጻሚዎች ጋር ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ እያደረጉ ነው የተባለ ሲሆን፥ ከጥቃት አድራሾቹም በርካቶቹ መሞታቸው እንዳልቀረ ገልጿል።

በተኩስ ልውውጡ ጊዜ አራት የአምቡላንስ ሰራተኞች መጎዳታቸውም ተነግሯል።

ምንጭ፦ www.reuters.com