የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የማስፋፊያ ስራውን አጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 4 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ  500 ሺህ ኩንታል ስኳር የነበረውን ዓመታዊ  የማምረት አቅም ወደ  2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማሳደግ የሚያስችለውን የማስፋፊያ ስራ አጠናቀቀ ።

 

የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ እንዳወቅ አብቴ ለፋና  ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት  እንደተናገሩት፥ ለማስፋፊያ ስራው 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል።

ሀገሪቱ በአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማብቂያ ላይ በዓመት ለማምረት ካቀደችው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ስኳር ውስጥ ፋብሪካው  17 በመቶውን ምርት እንደሚሸፍንም ነው የተናገሩት።

ከስኳር ተረፈ ምርት የሚገኘው የኢታኖልና የኤሌክትሪክ ሃይልም እንዲሁ ከስኳር ምርቱ ጎን ለጎን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፥ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ አዲስ የተገነባው የኢታኖል ማምረቻ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት በዓመት 8 ሚሊዮን ሊትር  የሆነው የማምረት አቅም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ ማብቂያ ላይ 20 ሚሊዮን ሊትር ይደርሳል ነው የተባለው።

ይህም ሀገሪቱ 2007 ላይ ልታመርት ካቀደችው 134 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል 15 በመቶውን  የሚሸፍን ይሆናል።

የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ከራሱ የስኳር ተረፈ ምርት በሚያመርተው የኤሌክትሪክ ሃይል የሚሸፍነው ፋብሪካው፥ ከዚህ ቀድም ያመነጭ ከነበረው ሰባት ሜጋ ዋት በተጨማሪ ማስፋፊያውን ተከትሎ 34 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት ይችላል።

20 ሜጋ ዋቱን ፋብሪካው ለራሱ ፍጆታ በማዋል ቀሪ 10 ሜጋ ዋት ሃይሉን ደግሞ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ብሄራዊ ቋት ያስገባል።

ለ20 ሺህ ሰራተኞች  ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠረው ፋብሪካው  6 ሺህ ሄክታር የነበረውን የሸንኮራ አገዳ እርሻ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ 21 ሺህ ሄክታር ለማድረስ አቅዶ እስካሁን 19 ሺህ ሄክታር በሸንኮራ አገዳ ልማት ሸፍኗል።

በመሰረት ገዛኸኝ