ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሀዋሳ ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተከብሯል::

ቀኑ በዓለም ለ17ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ "የሠላም፣ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶቻችንን በማጎልበት የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ መንግስት የወጣቱን ችግር በተለይም ስራ አጥነትን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፥ በዓሉ ሲከበር ወጣቶች በሠላም ግንባታ፣ በመቻቻልና በአብሮነት በመኖር ሀገራዊ ስሜትን የሚያጎለብቱና ብሔራዊ መግባባትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ፅጌረዳ ዘውዱ፥ በወጣቱ የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ ፌዴሬሽኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡

ወጣቶችን በግጭት አፈታት ላይ በማካተት የመፍትሔውና የውሳኔው አካል ማድረግ ይገባልም ነው ያለችው፡፡

በመድረኩ በዓሉን በሚመለከት በቀረበው ፅሑፍ ላይ ወጣቶች መወያየታቸውን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡