በአፋር ክልል ጉሊና ወረዳ በደረሰ የመብረቅ አደጋ አራት ሰዎች ሞቱ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ጉሊና ወረዳ ትናንት በደረሰ የመብረቅ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን አሊ ቡቶ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በአደጋው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በአምስት ሰዎች ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡

በወረዳው ሀሌገርቦ ቀበሌ ልዩ ቦታው ያፊኦ በተባለ ቦታ ላይ ትናንት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ በወደቀ መብረቅ ባልና ሚስትን ጨምሮ የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው አምስት ሰዎችም በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም ህክምና እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመብረቅ አደጋው ከሰዎች በተጨማሪም በአካባቢው በነበሩ አንድ የቀንድ ከብትና ፍየል መሞታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተያዘው የክረምት ወቅት በአፋር ክልል ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በተለያዩ ወረዳዎች ተደጋጋሚ የመብረቅ አደጋ መከሰቱን፥ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ቀደም ሲል መግለፁ ይታወሳል፡፡

ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ እዋ፣ ዱብቲ፣ ኩነባና ጭፍራ ወረዳዎች በደረሰ የመብረቅ አደጋ፥ የ13 ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ መገለጹም የሚታወስ ነው።

በአጠቃላይ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመብረቅ ተመተው የሞቱ ሰዎች ቁጥር የአሁኖቹን ጨምሮ 17 ደርሷል፡፡