በባህር ዳር ከተማ የተጣለ ቦምብ በሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህር ዳር ከተማ በቀበሌ 04 በብሄራዊ ሎተሪ የባህር ዳር ቅርንጫፍ አካባቢ ቅዳሜ ምሽት የተጣለ ቦምብ በሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው፥ አደጋው ትናንት ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ50 አካባቢ መድረሱን ተናግረዋል።

በደረሰው አደጋም በጉዞ ላይ የነበሩ ወንድና ሴት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት በመድረሱ በባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡን ለማሸበር ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግም በፀጥታ አካላት ሰፊ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ድርጊቱ የባህርዳርን ሰላም ለማደፍረስና ልማቷን ለማደናቀፍ ፍላጎት ባላቸው ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍና በተባባሪዎቻቸው የተፈፀመ ሳይሆን እንደማይቀርም ጠቁመዋል።

ሐምሌ 23 ቀን 2009 እና ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃት ለመፈፀም በሂደት ላይ የነበሩ 4 ተጠርጣሪዎች በፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ኮማንደሩ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይም ሐምሌ 30 ቀን 2009 በፔዳ መስመር ቦምብ ያፈነዱ 3 ዋና የድርጊቱ ተሳታፊዎችና ሁለት ተባባሪ አካላት በፀጥታ ሃይሉ ብርቱ ጥረት በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

የከተማዋን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ የፀጥታ አካላት ለሚያደርጉት ጥረት ህዝቡ ጥፋተኞችን በማጋለጥ የተለመደ ትብብሩን ማድረግ እንደሚገባው ኮማንደር ዋለልኝ አሳስበዋል።


ምንጭ፦ ኢዜአ