የመንግስታቱ ድርጅት በኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ተከትሎ የተፈጠረው አለመረጋጋት እንዲቆም ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኬንያ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ በሃገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋት እንዲቆም ጥሪ አቀረበ።

በኬንያ ምርጫ ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፋቸውን ተከትሎ የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል፥ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።

በዚህ ሳቢያም የኦዲንጋ ደጋፊዎች ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት ግጭት የ11 ሰዎች ህይዎት ማለፉ ተነግሯል።

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም ተቀናቃኝ ሃይሎች፥ ደጋፊዎቻቸው ከረብሻ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

ዋና ጸሃፊው፥ ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎቻቸው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ አለባቸው ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም የሃገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች ልዩነቶቻቸውን በመነጋገር ሊፈቱ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት ከዚህ በፊት በሃገሪቱ የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረው አይነት ግጭት እንዳይፈጠር ሲልም ስጋቱን ገልጿል።

በሃገሪቱ በ2007 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በተቀሰቀሰ ግጭት 1 ሺህ 1 መቶ ሰዎች ሲሞቱ፥ ከ6 መቶ ሺህ በላይ በላይ ኬንያውያን ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ አልጀዚራ