በአሜሪካ ቻርሎትስቪል ከተማ ዘረኝነትን በመቃወም አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ቻርሎትስቪል ከተማ ዘረኝነትን በመቃወም አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመ።

በተሽከርካሪ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት 19 ሰዎች ቆስለዋል ተብሏል።

ጥቃቱን ጀምስ ፊልድስ የተባለ የ20 አመት ወጣት ማድረሱን ፖሊስ ገልጿል፤ አሁን ላይም ወጣቱ በቁጥጥር ስር ውሏል ነው የተባለው።

ወጣቱ ተሽከርካሪውን ወደ ሰልፈኞቹ በመንዳት ጉዳቱን አድርሷልም ነው ያለው ፖሊስ።

በወቅቱ በወጣቱ ከተፈጸመው ጥቃት ባሻገር በነጭ ብሄርተኞችና በጥቁር ሰልፈኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት፥ ሌሎች 15 ሰዎች መጎዳታቸውም ተገልጿል።

የነጭ ብሄርተኛ አቀንቃኞቹ በሰልፉ ከሌላ ቦታ በመምጣት ችግር እንደፈጠሩም ነው የተነገረው።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ጥቃቱን አውግዘዋል።

ፕሬዚዳንቱ ጥላቻና መከፋፈሉ ሊቆም ይገባልም ብለዋል።

እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ በርካታ አሜሪካውያን ግን በፕሬዚዳንቱ ላይ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።

የእርሳቸው ፓርቲ አባላትም የፕሬዚዳንቱን አካሄድ ተችተዋል።

ለአፍቃሪ ነጮች መታየትና ማቆጥቆጥ የእርሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉም ነው በፕሬዚዳንቱ ላይ ትችታቸውን የሰነዘሩት።

 

 

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ