በህንድ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ 46 ሰዎች ሞቱ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት የሟቾቹ ቁጥር 46 ደረሰ።

በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው የሂማቻል ፕራዴሽ ግዛት የደረሰው አደጋው፥ ለሻይ እረፍት የቆሙ ሁለት አውቶብሶችን በፍርስራሽ ቀብሯቸዋል።

አውቶብሶቹም ዝናቡን ተከትሎ ከተራራ ላይ በወረደው የድንጋይና የጭቃ ናዳ ተወስደዋል።

ይህን ተከትሎም በአውቶብሶቹ ውስጥ የነበሩ መንገደኞችን በህይዎት ለማትረፍ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ፍለጋ ላይ ናቸው።

እስካሁንም የ46 ሰዎች አስከሬን ብቻ ሲገኝ፥ በጭቃ ናዳ የተወሰዱ ሰዎችን የመፈለጉ ስራም ቀጥሏል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች አምስት ሰዎችም የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ፖሊስ በበኩሉ በሂማሊያ ተራራ ግርጌ በምትገኘው ግዛት የደረሰው አደጋ በርካታ ቤቶችን ጠራርጎ በመውሰዱ የአደጋውን መጠን ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል ነው ያለው።

በህንድ ከሰኔ እስከ መስከረም ባለው ዝናባማ ወቅት የመሬት መንሸራተትና ከባድ የጎርፍ አደጋዎች የተለመዱ ናቸው።

 


ምንጭ፦ አልጀዚራ