የራያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በ264 ሚሊየን ብር ባለፈው አመት የተጀመረው የራያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ምዕራፍ የግንባታ ስራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ።

የዩኒቨርሲቲው ኘሬዚዳንት ኘሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ በመጀመሪያው ምዕራፍ የግንባታ ስራ የተማሪዎች መማሪያና መኝታ ክፍሎች፣ የመምህራንና ሰራተኞች ቢሮዎችን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 22 ህንፃዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።

ቤተ-መጻህፍት፣ የተማሪዎች መመገቢያና መሰብሰቢያ አዳራሽ የመሳሰሉ አገልግሎት መስጫዎችም ተገንብተው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ የህንጻዎቹ ግንባታ መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ ከአራት ወር በላይ ዘግይቷልም ነው ያሉት።

በግንባታ ላይ የሚሰማሩ የአካባቢው ወጣቶችን በማህበራት የማደራጀት ስራ ጊዜ በመውሰዱ ስራው ለተወሰነ ወራት ተጓቶ መቆየቱንም አስታውሰዋል፤ አሁን ርክክብ እየተፈጸመ መሆኑን በመጥቀስ።

መጻህፍትን ጨምሮ ለመማር ማስተማር ስራ የሚያስፈልግ የውስጥ ቁሳቁስ የማሟላት ስራም በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይም ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው 121 መምህራን በመቅጠር ለመማር ማስተማሩ ስራ እንዲዘጋጁ ተደርጓል ብለዋል።

በአዲሱ የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮና ማህበረሰብ ሳይንስ፣ በእርሻ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የትምህርት ክፍል በተካተቱ 18 የትምህርት አይነቶች፥ 1 ሺህ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ስራውን እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

ከፌደራል መንግስት በተመደበ 364 ሚሊየን ብር በጀት የራያ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛው ዙር የማስፋፊያ ግንባታ በመጭው መስከረም 2010 ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።