ፓርቲዎች የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ከመንግስት እንዲያገኙ የሚያስችሉና ሌሎች አዳዲስ አንቀፆች እንዲካተቱ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) 16 ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ስራ ማስኬጃ ገንዘብ ከመንግስት እንዲያገኙ የሚያስችሉና ሌሎች ተጨማሪ አንቀፆች በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ እንዲካተቱ ተስማምተዋል፡፡

በመጨረሻው የድርድር ዙር ከአንቀፅ 42 እስከ 63 ያሉ ድንጋጌዎች ላይ ዛሬ የተደራደሩ ሲሆን፥ ሶስት ንፁሳን አንቀፆች እንዲጨመሩ አንድ ንዑስ አንቀፅ እንዲሰረዝ ነው የተስማሙት፡፡

እንዲጨመሩ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው አንቀፆች ለፓርቲዎች የሚደረግ ፋይናንስ ድጋፍን የተመለከቱ መሆናቸውን፥ የድርድር ሚድያ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ደግፌ ቡላ ተናግረዋል።

በስምምነቱ መሰረት በአዋጁ አንቀፅ 42 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ 'ሐ' እና 'መ' ተብለው ሁለት ድንጋጌዎች ተጨምረዋል።

ንዑሳን አንቀፆቹ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ስራ ማስኬጃ የፋይናንስ ድጋፍ የሚገኙበትን መስፈርት የሚደነግጉ ናቸው።

በዚህም መሰረት ፓርቲዎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙት አንደኛ ባገኙት ድምፅ እና ባስመዘገቡት እጩ ብዛት፥ ሁለተኛ ፓርቲዎቹ በፌደራልም ሆነ በክልል ምክር ቤት ባላቸው የወንበር ብዛት መስፈርት እንዲሆን ተወስኗል።

የሚሰጠው ድጋፍ የሚከፋፈልበት ሁኔታና ጊዜ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎቹ ጋር ተመካክሮ፥ በሚያወጣው መመሪያ እንዲወስን የሚደነግግ ንዑስ አንቀፅ ተካቷል።

ምርጫ ቦርድ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሳይፈፀሙ ቢቀሩ በስልጣኑ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስድ ሲሆን፥ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አፈፃፀም ከፍቶ እንዲያስፈፅም ስልጣን የሚሰጥ ንዑስ አንቀፅም ተጨምሯል፡፡

ፓርቲዎቹ በአጠቃላይ በአዋጁ ላይ ያደረጉት ድርድር በስምምነት ቢጠናቀቅም፥ የተወሰኑ ፓርቲዎች በተወሰኑ አንቀፆች ላይ ልዩነት እንዲመዘገብላቸው ጠይቀዋል።

የድርድሩ ሚድያ ኮሚቴ አባል አቶ ገብሩ በርሄ፥ ፓርቲዎቹ ልዩነት ያስመዘገበቡባቸውን አንቀፆች በቃለ ጉባኤ ከመያዝ ውጪ ስምምነቱን አይሽርም ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ ድርድራቸውን በስምምነት ያጠናቀቁት ፓርቲዎቹ፥ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ በምርጫ አዋጁ 532/99 ላይ ድርድራቸውን ለመቀጠል ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

ፓርቲዎቹ 63 አንቀፆች ባሉት አዋጅ ላይ ለሶስት ሳምንታት ከተደራደሩ በኋላ 13 አንቀፆችና ንኡሳን አንቀፆች እንዲጨመሩ፥ 13 አንቀፆች እንዲሻሻሉ እንዲሁም የተወሰኑት እንዲሰረዙ ስምምነት ላይ በመድረስ አጠናቀዋል፡፡

 

 

 

 

 

በዳዊት መስፍን