በአዲስ አበባ ጉድለት የተገኘባቸው 19 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ተዘጉ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 5 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በቂ የማለማመጃ ተሽከርካሪዎች ካለማቅረብ ጀምሮ ሌሎች ጉድለቶች የተገኙባቸው 19 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ተዘጉ።

በሀገሪቱ ከሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል 80 በመቶው በአሽከርካሪዎች የብቃት ማነስ ምክንያት የሚከሰት መሆኑን የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ለችግሩ የማሰልጠኛ ተቋማቱ ብቃት ማነስ ምንጭ ሲሆን፥ በቂ የማለማመጃ ተሽከርካሪ ማቅረብ አለመቻልን ጨምሮ ትምህርት ላልወሰደ ተለማማጅ በገንዘብ መንጃ ፈቃድ እስከ መስጠት የደረሰ ህገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ስለመኖራቸው ሰልጣኞች ያነሳሉ።

በአዲስ አበባ 66 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን፥ የአዲስ አበባ አሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፍቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣንም ባደረገው ግምገማ ጉድለቶች ማግኘቱን ገልጿል።

በድንገተኛ ፍተሻ እና በየሁለት አመቱ ከሚካሄደው ግምገማ በተገኘው ውጤትም መሰረት ከ66ቱ ተቋማት መካከል 19 እንዲዘጉ መደረጉን፥ የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ፉፋ ተናግረዋል።

በጊዜያዊነት አሽከርካሪዎችን ከማሰልጠን ከታገዱት 19 ተቋማት መካከል አስራ አምስቱ ለሁለት ወራት ቀሪዎቹ አራት ተቋማት ደግሞ ለሶስት ወራት አገልግሎት እንዳይሰጡ ተወስኗል።

ተቋማቱ እንዲህ አይነት እርምጃ የተወሰደባቸው ከማሰልጠኛ ተሸከርካሪ አቅርቦት ጀምሮ ሌሎች በርካታ ጉድለቶች ስለተኙባቸው መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

በጊዜያዊነት እንዲዘጉ የተወሰነባቸው ተቋማት የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላታቸው እስከሚረጋገጥ እና የተወሰነባቸው የቅጣት ጊዜ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ምንም አይነት ስልጠና መስጠትም ሆነ አዲስ ሰልጣኞችን መቀበል አይችሉም።

ተቋማቱ በእጃቸው ያለውን ሰልጣኞች ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላም እንደ ቅጣታቸው መጠን ለሁለት እና ሶስት ወራት ይዘጋሉም ነው ያሉት።

በጊዜያዊነት እንዲዘጉ ከተደረጉት ተቋማት በተጨማሪም ለ34 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የመጀመሪያ እና የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

ከ34ቱ ተቋማት ውስጥም ሰባቱ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው 27ቱ ደግሞ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ነው የተሰጣቸው።

ባለስልጣኑ በዙር ካደረጋቸው ግምገማዎች በተጨማሪም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ እና ተቋማቱ ላይም ክትትል በማድረግ፥ 47 ያህል ሰልጣኞችን ህጋዊ ባልሆነ መልኩ እና ስልጠናቸውን ሳያጠናቅቁ ለፈተና ሊያስቀምጡ የሞከሩ ሶስት ተቋማት ላይም እርምጃ ወስዷል።

በዚህም ኬቢ ቁጥር ሶሰት 40 ሰልጣኝ፣ ይሄነው ማስተዋል 2 ሰልጣኝ እንዲሁም ፎርዊል 5 ሰልጣኞችን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሊያስፈትኑ ሲሉ ተይዘው ላልተወሰነ ጊዜ አንዲዘጉ ተደርጓል።

በዙር ግምገማውም ሆነ በተጨማሪ ክትትል እርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት በተሰጣቸው ደብዳቤ መሰረት፥ የተገኘባቸውን ክፍተት እስከተሰጣቸው ወር ድረስ ካስተካከሉ ወደ ስራቸው የሚመለሱ ሲሆን ማስተካከል ባልቻሉት ላይ ግን እርምጃው የሚቀጥል ይሆናል።

 

 

በዙፋን ካሳሁን