በደቡብ ሱዳን ፓጋክ በመንግስት ወታደሮችና አማፂያን መካከል ግጭት መከሰቱ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ሱዳኗ ፓጋክ በመንግስት ወታደሮች እና በአማፂያን መካከል ከፍተኛ ግጭት መከሰቱ ተሰምቷል።

ግጭቱ የተከሰተው የሬክ ማቻር ታማኝ ሀይሎች በደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮች ላይ መውሰድ በጀመሩት የአፀፋ ምክንያት መሆኑንም አማፂያኑ አስታውቀዋል።

የአማፂያኑ ቃል አቀባይ ላም ፓውል ገበሪኤል፥ ባሳለፍነው ሰኞ የመንግስት እጅ የገባችውን የፓጋክ ግዛትን መልሶ በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው ጥቃቱ የተከፈተው ብለዋል።

“የደቡብ ሱዳን መንግስት ፓጋከን ከስድስት ቀናት በፊት ነው የነጠቀን፣ ከዚህ በመነሳትም በመንግስት ጦር ላይ ጥቃት ለመፈፀም ወሰንን” በማለትም አስታውቀዋል።

“ምክንያቱ ደግሞ ፓጋክ የኛ ዋነኛ ማእከል ነው፤ ስለወሰዱብን ለማስመለስ ነው እርምጃውን መውሰድ የጀመርነው” ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦር ቃል አቀባይ ጋትሉዋክ ጆክ እና የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንግ ጋዪ፥ ከአማፂያን ጋር ጦርነት መግጠማቸውን አረጋግጠዋል።

ምንጭ፦ www.reuters.com