በሀዋሳ ከባለ 3 እግር ታክሲ ማህበራት በየወሩ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ተጠቀሚ እየሆንን አይደለም- የማህበራቱ አባላት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀዋሰ ከተማ ከባለ ሶስት እግር ታክሲ ማህበራት በየወሩ የሚሰበሰበው የመዋጮ ገንዘብ በአግባቡ ተጠቃሚ እየሆንን አይደለም ይላሉ በከተማዋ የሚገኙ የማህበራቱ አባላት።

እስካሁን ከተዋጣው ገንዘብ ውስጥም ምን ያህሉ እንዳለ ተፈትሾ በፍላጎታችን መሰረት እንድንጠቀም ሊደረግ ይገባል ሲሉም የማህበራቱ አባላት ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አቅርበዋል።

የማህበራቱ አባላት በየወሩ ከእያንዳንዱ ሰው እስከ 45 ብር ለመዋጮ በሚል ይሰበሰባል የሚሉ ሲሆን፥ ይህም በዓመት ከ1 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ያሳያል ይላሉ።

“በአሁኑ ወቅት የገንዘቡ መጠን ምን ያክል እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም፤ ለመዋጮ የሚሰበሰበው ገንዘብ መጠን ታውቆ አዳዲስ ታክሲዎችን በመግዛት ተጠቃሚ እንድንሆን መደረግ አለበት” ሲሉም ይናገራሉ።

ከአንድ አመት በላይ ቅሬታውን ሲያጣራ የነበረው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተቀመጠውን የገንዘብ መጠን ለማወቅ ቢጥርም መረጃ ማግኘት አልቻለም።

የታክሲ አንድ ማህበራቶች የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አብዱ መሀመድ፥ ስለ ገንዘቡ መጠን ከመናገር ተቆጥበዋል።

የተቀመጠውን ገንዘብ ለማህበራቱ በየጊዜው ይፋ ከማድረጋችን ባለፈ በአባላቱ ፍላጎት መሰረት ወደ ከተማ በማስገባት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራን ሉም ተናግረዋል።

“በገንዘቡ ላይ በየዓመቱ የኦዲት ስራ ይከናወናል” ያሉት አቶ አብዱ፥ ይህንን የሚያረጋግጠው ደግሞ የከተማው የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ነው ይላሉ።

የከተማው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ማህበራቱ ያላቸውን የገንዘብ መጠን አላውቅም ይላል፡፡

የሀዋሳ ከተማ የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አቶ ዘሪሁን ሰለሞን፥ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚቀርብ ቅሬታ ካለ ተጣርቶ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።
ቀጣይ በአባላቱ ፍላጎት መሰረት ተግባራዊ ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።

በብርሀኑ በጋሻው